2 ነገሥት 12:9-15 NASV

9 ከዚያም ካህኑ ዮዳሄ አንድ ሣጥን ወስዶ በመክደኛው ላይ ቀዳዳ አበጀለት፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሚያስገባው በስተ ቀኝ በኩል በመሠዊያው አጠገብ አኖረው። በራፉን የሚጠብቁት ካህናትም ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጣውን ገንዘብ በሙሉ በሣጥኑ ውስጥ ያስገቡ ነበር።

10 በሣጥኑም ውስጥ ብዙ ገንዘብ መኖሩን በሚያዩበት ጊዜ ሁሉ፣ የንጉሡ ጸሐፊና ሊቀ ካህናቱ መጥተው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የገባውን ገንዘብ ቈጥረው በየከረጢቱ በማስገባት ቋጥረው ያኖሩት ነበር።

11 የገንዘቡ ልክም ተመዝኖ ከታወቀ በኋላ፣ የቤተ መቅደሱን ሥራ በኀላፊነት እንዲያሠሩ ለተመደቡት ሰዎች ገንዘቡን ያስረክቧቸዋል፤ ይህም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለሚሠሩ አናጢዎችና ግንበኞች፣

12 ለድንጋይ ጠራቢዎችና ለድንጋይ ቅርጽ አውጭዎች የሚከፈል እንዲሁም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለሚታደስበት ዕንጨትና ጥርብ ድንጋይ መግዣ የሚውል ነበር።

13 ለቤተ መቅደሱ ከገባው ገንዘብ ግን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግልጋሎት ለሚውሉ የብር ጽዋዎች፣ መኰስተሪያዎች፣ ድስቶች፣ መለከቶችና ወይም ለሌሎች የወርቅም ሆነ የብር ዕቃዎች መሥሪያ አልዋለም፤

14 የተከፈለው ግን ቤተ መቅደሱን ለሚያድሱ ሠራተኞች ብቻ ነበር።

15 ለሠራተኞቹ እንዲከፍሉ ገንዘቡ የተሰጣቸው ሰዎች ፍጹም ታማኞች በመሆናቸው ተቈጣጣሪ ማድረግ አላስፈለጋቸውም ነበር።