2 ነገሥት 13:2-8 NASV

2 እርሱም የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ያሳተበትን ኀጢአት በመከተል በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ፤ ከዚህ ድርጊቱም አልተመለሰም።

3 የእግዚአብሔር ቊጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፤ ስለዚህ የሶርያ ንጉሥ አዛሄልና ልጁ ቤንሃዳድ በነበሩበት ዘመን ሁሉ አሳልፎ በእጃቸው ሰጣቸው።

4 ከዚያም ኢዮአካዝ እግዚአብሔርን ለመነ፤ እግዚአብሔርም የሶርያ ንጉሥ እስራኤልን እንዴት አድርጎ እንዳስጨነቀ አይቶአልና ልመናውን ሰማው።

5 ስለዚህ እግዚአብሔር ለእስራኤል የሚታደጋቸውን ሰው ሰጠ፤ እነርሱም ከሶርያውያን ጭቈና ተላቀቁ፤ እንደ ቀድሞውም በየድንኳናቸው መኖር ጀመሩ፤

6 ይሁን እንጂ እስራኤልን ካሳተው ከኢዮርብዓም ቤት ኀጢአት አልተመለሱም፤ በዚያው ገፉበት። የአሼራም ምስል ዐምድ በሰማርያ መመለኩ ቀጠለ።

7 ከኢዮአካዝ ሰራዊት የተረፈው ዐምሳ ፈረሰኞች፣ ዐሥር ሠረገሎችና ዐሥር ሺህ እግረኛ ወታደር ብቻ ነው፤ ይህ የሆነበትም ምክንያት የሶርያ ንጉሥ የቀረውን ስለ አጠፋውና እንደ ዐውድማ ብናኝ ስለ አደረገው ነበር።

8 ኢዮአካዝ በዘመነ መንግሥቱ ያከናወነው ሌላው ሥራ፣ ያደረገውና የፈጸመውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?