2 ነገሥት 13:7-13 NASV

7 ከኢዮአካዝ ሰራዊት የተረፈው ዐምሳ ፈረሰኞች፣ ዐሥር ሠረገሎችና ዐሥር ሺህ እግረኛ ወታደር ብቻ ነው፤ ይህ የሆነበትም ምክንያት የሶርያ ንጉሥ የቀረውን ስለ አጠፋውና እንደ ዐውድማ ብናኝ ስለ አደረገው ነበር።

8 ኢዮአካዝ በዘመነ መንግሥቱ ያከናወነው ሌላው ሥራ፣ ያደረገውና የፈጸመውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

9 ኢዮአካዝ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ተቀበረ። ልጁ ዮአስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

10 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ ዘመን፣ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት፣ የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በሰማርያ ከተማ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ዐሥራ ስድስት ዓመትም ገዛ።

11 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት ሁሉ አልራቀም፤ በዚያው ገፋበት።

12 ዮአስ በዘመነ መንግሥቱ ያከናወነው ሌላ ሥራ፣ ያደረገውና የፈጸመው ሁሉ እንዲሁም በይሁዳ ንጉሥ በአሜስያስ ላይ ያካሄደው ጦርነት ጭምር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?።

13 ዮአስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ኢዮርብዓም በእግሩ ተተክቶ በዙፋኑ ተቀመጠ። ዮአስም በሰማርያ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ።