2 ነገሥት 14:20-26 NASV

20 ሬሳውም በፈረስ ተጭኖ መጥቶ በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር በኢየሩሳሌም ተቀበረ።

21 ከዚያም የይሁዳ ሕዝብ በሙሉ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት የሆነውን ዓዛርያስን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፋንታ አነገሡት።

22 አሜስያስ ከአባቶቹ ጋር ካንቀላፋ በኋላ ኤላትን እንደ ገና ሠርቶ ወደ ይሁዳ የመለሳት ይኸው ዓዛርያስ ነበር።

23 የኢዮስያስ ልጅ አሜስያስ በይሁዳ በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት፣ የእስራኤል ንጉሥ የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም በሰማርያ ነገሠ፤ አርባ አንድ ዓመትም ገዛ።

24 በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።

25 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በጋትሔፌር ነቢይ፣ በአማቴ ልጅ በባሪያው በዮናስ አማካይነት እንደ ተናገረው፣ ከሐማት መተላለፊያ አንሥቶ እስከ ሙት ባሕር ድረስ የነበረውን የእስራኤልን ድንበር ያስመለሰ ኢዮርብዓም ነው።

26 ባሪያም ይሁን ነጻ ዜጋ፣ በእስራኤል የሚኖር ሁሉ እንዴት እጅግ ይሠቃይ እንደ ነበር እግዚአብሔር አየ፤ የሚረዳቸውም አልነበረም።