3 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ፤ ነገር ግን አባቱ ዳዊት እንደ አደረገው ዐይነት አልነበረም፤ በማናቸውም ረገድ የአባቱን የኢዮአስን ፈለግ ተከተለ።
4 በየኰረብታው ላይ ያሉት ማምለኪያዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በየኰረብታው ላይ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር።
5 አሜስያስ መንግሥቱን አጽንቶ ከያዘ በኋላ፣ ንጉሡን አባቱን የገደሉትን ሹማምት ገደላቸው፤
6 ይሁን እንጂ በሙሴ የሕግ መጽሐፍ እግዚአብሔር፣ “እያንዳንዱ በራሱ ኀጢአት ይገደል እንጂ አባቶች በልጆቻቸው፣ ልጆችም በአባቶቻቸው ኀጢአት አይገደሉ” ሲል ያዘዘ በመሆኑ፣ የነፍሰ ገዳዩን ልጆች አልገደላቸውም።
7 የጨው ሸለቆ በተባለው ቦታ ዐሥር ሺህ ኤዶማውያንን ድል ያደረገ፣ ሴላን በጦርነት የያዘና እስከ ዛሬም ድረስ ዮቅትኤል ተብላ የምትጠራበትን ስም ያወጣላት አሜስያስ ነው።
8 ከዚያም አሜስያስ የኢዩ የልጅ ልጅ፣ የኢዮአካዝ ልጅ ወደ ሆነው ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ዮአስ፣ “ናና ፊት ለፊት ይዋጣልን” ሲል መልእክተኞች ላከበት።
9 የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ግን ለይሁዳ ንጉሥ ለአሜስያስ እንዲህ ሲል ላከበት፤ “አንድ የሊባኖስ ኵርንችት፣ ለአንድ የሊባኖስ ዝግባ፣ ‘ሴት ልጅህን ለልጄ በሚስትነት ስጠው’ አለው፤ ከዚያም አንድ የሊባኖስ ዱር አውሬ መጥቶ ኵርንችቱን በእግሩ ረገጠው።