2 ነገሥት 15:1-7 NASV

1 የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአሜስያስ ልጅ ዓዛርያስ ነገሠ።

2 ሲነግሥም ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ አምሳ ሁለት ዓመት ገዛ። እናቱም ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።

3 አባቱ አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ ዓዛርያስም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ።

4 ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረቡንና እጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር።

5 እግዚአብሔርም ንጉሡን እስከሚሞትበት ቀን ድረስ በለምጽ መታው፤ በተለየ ቤትም ይኖር ነበር። በዚያን ጊዜ ቤተ መንግሥቱን በኀላፊነት የሚመራውና የአገሩንም ሕዝብ የሚያስተዳድረው የንጉሡ ልጅ ኢዮአታም ነበር።

6 በዓዛርያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

7 ዓዛርያስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ በአባቶቹ መቃብር አጠገብ ቀበሩት። ልጁ ኢዮአታምም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።