2 ነገሥት 15:14-20 NASV

14 የጋዲ ልጅ ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ ወደ ሰማርያ በመሄድ አደጋ ጥሎ የኢያቤስን ልጅ ሰሎምን ገደለው፤ ከዚያም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

15 በሰሎም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራና የጠነሰሰውም ሤራ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎአል።

16 በዚያን ጊዜም ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ በቲፍሳና በከተማዪቱ ነዋሪዎች ላይ ሁሉ፣ በአካባቢዋም ጭምር አደጋ ጣለ፤ ይህን ያደረገውም የከተማዪቱን በሮች ለመክፈት ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ነበር፤ ቲፍሳን መታት፤ የነፍሰጡሮችንም ሆድ ሁሉ ቀደደ።

17 የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት፣ የጋዲ ልጅ ምናሔም በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በሰማርያ ተቀም ጦም ዐሥር ዓመት ገዛ።

18 በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ በዘመኑም ሁሉ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።

19 ከዚያም የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌ ልሶርፀ ምድሪቱን ወረረ፤ ምናሔም ርዳታውን ለማግኘትና በመንግሥቱ ላይ ያለውን ይዞታ ለማጽናት ሲል፣ አንድ ሺህ መክሊት ብር ሰጠው።

20 ምናሔም ገንዘቡ እንዲዋጣ ያደረገው ከእስራኤል ሲሆን፣ ይህንንም ያደረገው ለአሦር ንጉሥ ይሰጥ ዘንድ እያንዳንዱ ሀብታም አምሳ፣ አምሳ ሰቅል ብር እንዲያዋጣ በማስገደድ ነበር። ስለዚህ የአሦር ንጉሥ በዚያች አገር አልቈየም፤ ተመልሶ ሄደ።