2 ነገሥት 15:25-31 NASV

25 ከጦር አለቆቹ አንዱ የሆነው የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ አሤረበት፤ አምሳ የገለዓድ ሰዎች ይዞ በመሄድ፣ ሰማርያ ቤተ መንግሥት ባለው ምሽግ ፋቂስያስን ከአርጎብና ከአርያ ጋር ገደለው፤ በእግሩም ተተክቶ ነገሠ።

26 በፋቂስያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸመውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎአል።

27 የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በአምሳ ሁለተኛው ዓመት የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በሰማርያ ከተማ፣ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ሃያ ዓመትም ገዛ።

28 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።

29 በእስራኤል ንጉሥ በፋቁሔ ዘመን፣ የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር መጥቶ ዒዮን፣ አቤልቤትመዓካን፣ ያኖዋን፣ ቃዴስንና ሐጾርን፣ ገለዓድንና ገሊላን፣ የንፍታሌምንም ምድር ጭምር ያዘ። ሕዝቡንም ማርኮ ወደ አሦር ወሰደው።

30 ከዚያም የኤላ ልጅ ሆሴዕ በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ ላይ አሤረበት፤ አደጋ ጥሎም ገደለው፤ የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም በነገሠ በሃያኛው ዓመትም ሆሴዕ በፋቁሔ እግር ተተክቶ ነገሠ።

31 በፋቁሔ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸማቸውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?