2 ነገሥት 15:29-35 NASV

29 በእስራኤል ንጉሥ በፋቁሔ ዘመን፣ የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር መጥቶ ዒዮን፣ አቤልቤትመዓካን፣ ያኖዋን፣ ቃዴስንና ሐጾርን፣ ገለዓድንና ገሊላን፣ የንፍታሌምንም ምድር ጭምር ያዘ። ሕዝቡንም ማርኮ ወደ አሦር ወሰደው።

30 ከዚያም የኤላ ልጅ ሆሴዕ በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ ላይ አሤረበት፤ አደጋ ጥሎም ገደለው፤ የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም በነገሠ በሃያኛው ዓመትም ሆሴዕ በፋቁሔ እግር ተተክቶ ነገሠ።

31 በፋቁሔ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸማቸውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

32 የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ የይሁዳ ንጉሥ የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም ነገሠ።

33 ሲነግሥም ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ ኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፤ እናቱም የሳዶቅ ልጅ ስትሆን፤ ኢየሩሳ ትባል ነበር።

34 አባቱ ዖዝያን እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ።

35 ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር። ኢዮአታም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የላይኛውን በር መልሶ ሠራ።