14 ይሁን እንጂ እነዚህም አልሰሙም፤ እግዚአብሔር አምላካቸውን እንዳልታመኑበት እንደ አባቶቻቸው ዐንገታቸውን አደነደኑ።
15 ሥርዐቱንና ከአባቶቻቸው ጋር የገባውን ኪዳን፣ ለእነርሱም የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ናቁ፤ ከንቱ ጣዖታትን ተከትለው ራሳቸውም ከንቱ ሆኑ፤ እግዚአብሔር፣ “እነርሱ የሚያደርጉትን እንዳታደርጉ” ብሎ ቢያዛቸው እንኳ በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብ ተከተሉ፤ እግዚአብሔር እንዳያደርጉ የከለከላቸውንም ፈጸሙ እንጂ አልተዉም።
16 አምላካቸው እግዚአብሔር ያዘዛቸውን ሁሉ አልፈጸሙም፤ አቅልጠውም ሁለት የጥጃ ምስልና የአሼራን ምስል ዐምድ ሠሩ፤ ለሰማይ ከዋክብት ሰገዱ፤ በኣልን አመለኩ፤
17 እንዲሁም ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። ጥንቈላና መተት አደረጉ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር ለማድረግ ራሳቸውን ሸጡ፤ ለቊጣም አነሣሡት።
18 ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ እጅግ ተቈጣ፤ የይሁዳ ነገድ ብቻ ሲቀር እስራኤልን ከፊቱ አራቀ።
19 ይሁዳም ቢሆን ከእስራኤል የተቀበለውን ልማድ ተከተለ እንጂ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልጠበቀም።
20 ስለዚህ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ሁሉ ተዋቸው፤ አስጨነቃቸው፤ ከፊቱ እስኪያስወግዳቸውም ድረስ በማራኪዎቻቸው እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።