1 ንጉሥ ሕዝቅያስ ይህን ሲሰማ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለብሶም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ገባ።
2 ከዚያም የቤተ መንግሥቱን አዛዥ ኤልያቄምን፣ ጸሓፊውን ሳምናስንና ዋና ዋናዎቹን ካህናት ማቅ ለብሰው ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲሄዱ ሁሉንም ላካቸው።
3 እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ሕዝቅያስ የሚለው ይህ ነው፤ ‘እንግዲህ ይህች ዕለት የመከራ፣ የዘለፋና የውርደት ቀን ናት፤ ይህችም ቀን ልጆች ሊወለዱ ምጥ እንዳፋፋመበት፣ ነገር ግን ለመገላገል ዐቅም እንደታጣበት ሰዓት ናት።
4 ሕያው እግዚአብሔርን ያንቋሽሽ ዘንድ በጌታው በአሦር ንጉሥ የተላከውን የጦር አዛዡን ቃል ሁሉ እግዚአብሔር አምላክህ ሰምቶ ይሆናልና፣ ስለሰማውም ቃል እግዚአብሔር እንዲገሥጸው በሕይወት ስለተረፉት ወገኖቻችን እባክህ ጸልይ።”
5 የንጉሥ ሕዝቅያስ ሹማምት ወደ ኢሳይያስ በመጡ ጊዜ፣
6 ኢሳይያስ እንዲህ አላቸው፤ “ለጌታችሁ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤ ‘እንግዲህ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ “የአሦር ንጉሥ አገልጋዮች በእኔ ላይ የወረወሯቸውን የስድብ ቃላት በመስማትህ አትፍራ።
7 እነሆ፣ አንድ ዐይነት መንፈስ አሳድርበታለሁ፤ የሆነ ወሬም ሲሰማ ወደ አገሩ ይመለሳል፤ እዚያም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርገዋለሁ።’ ”