2 ነገሥት 2:12-18 NASV

12 ኤልሳዕም ይህን አይቶ፣ “አባቴ አባቴ የእስራኤል ሠረገሎችና ፈረሰኞች!” ብሎ ጮኸ፤ ዳግመኛም ኤልያስን አላየውም፤ ከዚያም የገዛ ልብሱን ይዞ ከሁለት ቦታ ቀደደ።

13 እርሱም ከኤልያስ የወደቀውን ካባ አነሣ፤ ተመልሶም በዮርዳኖስ ወንዝ ዳር ቆመ።

14 ከኤልያስ፣ የወደቀውንም ካባ ይዞ ውሃውን መታና፣ “የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው?” አለ። ውሃውን ሲመታውም በግራና በቀኝ ተከፍሎለት ተሻገረ።

15 ከኢያሪኮም መጥተው ይህን ያዩ የነበሩት የነቢያት ወገኖች፣ “የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ዐርፎአል” አሉ፤ ሊያገኙትም ሄደው በፊቱ ወደ መሬት ዝቅ ብለው እጅ ነሡ።

16 ከዚያም፣ “እነሆ እኛ አገልጋዮችህ እዚህ አምሳ ጠንካራ ሰዎች አሉን፤ ምናልባትም የእግዚአብሔር መንፈስ ጌታህን አንሥቶ ከአንዱ ተራራ ላይ አስቀምጦት ወይም ከአንዱ ሸለቆ አግብቶት ይሆናልና እስቲ ሄደው ይፈልጉት” አሉት። ኤልሳዕም፣ “አይሆንም፤ አትላኳቸው” አለ።

17 አይሆንም ለማለት ዕፍረት እስኪሰማው ድረስ ግድ አሉት፤ ስለዚህ፣ “በሉ እንግዲያው ላኳቸው” አለ። እነርሱም አምሳ ሰዎች ላኩ፤ ሰዎቹም ሦስት ቀን ሙሉ ፈልገው ሳያገኙት ቀሩ።

18 በኢያሪኮ ቈይቶ ወደ ነበረው ወደ ኤልሳዕ በተመለሱም ጊዜ፣ “ቀድሞውንስ ቢሆን አትሂዱ ብያችሁ አልነበረምን?” አላቸው።