2 ነገሥት 2:9-15 NASV

9 ከተሻገሩ በኋላም ኤልያስ ኤልሳዕን፤ “ከአንተ ከመወሰዴ በፊት ምን ላደርግልህ እንደምትፈልግ ንገረኝ” አለው።ኤልሳዕም፣ “መንፈስህ በዕጥፍ እንዲያድ ርብኝ እለምንሃለሁ” ብሎ መለሰ።

10 ኤልያስም፣ “አስቸጋሪ ነገር ጠይቀሃል፤ ይሁን እንጂ እኔ ከአንተ ስወሰድ ብታየኝ፣ እንዳልከው ይሆንልሃል፤ ያለበለዚያ ግን አይሆንም” አለው።

11 እያዘገሙም ሲነጋገሩ ሳለ፣ የእሳት ሠረገላና የእሳት ፈረሶች ድንገት በመካከላቸው ገብተው ሁለቱን ለዩአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ዐረገ።

12 ኤልሳዕም ይህን አይቶ፣ “አባቴ አባቴ የእስራኤል ሠረገሎችና ፈረሰኞች!” ብሎ ጮኸ፤ ዳግመኛም ኤልያስን አላየውም፤ ከዚያም የገዛ ልብሱን ይዞ ከሁለት ቦታ ቀደደ።

13 እርሱም ከኤልያስ የወደቀውን ካባ አነሣ፤ ተመልሶም በዮርዳኖስ ወንዝ ዳር ቆመ።

14 ከኤልያስ፣ የወደቀውንም ካባ ይዞ ውሃውን መታና፣ “የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው?” አለ። ውሃውን ሲመታውም በግራና በቀኝ ተከፍሎለት ተሻገረ።

15 ከኢያሪኮም መጥተው ይህን ያዩ የነበሩት የነቢያት ወገኖች፣ “የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ዐርፎአል” አሉ፤ ሊያገኙትም ሄደው በፊቱ ወደ መሬት ዝቅ ብለው እጅ ነሡ።