14 ከዚያም ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ሕዝቅያስ ሄዶ፣ “እነዚያ ሰዎች ምን አሉህ? የመጡትስ ከወዴት ነው?” ሲል ጠየቀው።ሕዝቅያስም መልሶ፣ “የመጡት ከሩቅ አገር ከባቢሎን ነው” አለው።
15 ነቢዩም፣ “በቤተ መንግሥትህ ምን ምን አዩ?” ሲል ጠየቀው።ሕዝቅያስም፣ “በቤተ መንግሥቴ ያለውን ሁሉ አይተዋል፤ በግምጃ ቤቶቼ ሳላሳያቸው የቀረ ምንም ነገር የለም” አለ።
16 ከዚያም ኢሳይያስ ሕዝቅያስን እንዲህ አለው፤ “የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤
17 በቤተ መንግሥትህ ያለው ሁሉ አባቶችህም እስከ ዛሬ ድረስ ያከማቹት በሙሉ ወደ ባቢሎን የሚወሰድበት ጊዜ በርግጥ ይመጣል፤ አንዳች የሚቀር ነገር የለም ይላል እግዚአብሔር።
18 የሥጋህ ቁራጭ የዐጥንትህ ፍላጭ ከሚሆኑት፣ ከምትወልዳቸው ልጆችህ አንዳንዶቹ በምርኮ ይወሰዳሉ፤ በባቢሎንም ቤተ መንግሥት ጃንደረቦች ይሆናሉ።”
19 ሕዝቅያስም፣ “የተናገርኸው የእግዚአብሔር ቃል መልካም ነው” ሲል መለሰ፤ “እኔ እስካለሁ ድረስ ሰላምና ጸጥታ ከተገኘ የሆነው ይሁን” ብሎ አስቦአልና።
20 በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ሁሉ ኵሬውንና ውሃውን ወደ ከተማዪቱ ያመጣበትን የመሬት ለመሬት ቦይ እንዴት አድርጎ እንደ ሠራው በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?