2 ነገሥት 4:2-8 NASV

2 ኤልሳዕም፣ “ታዲያ እኔ ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ? በቤትሽ ምን እንዳለ ንገሪኝ” አላት።እርሷም፣ “አገልጋይህ ከጥቂት ዘይት በቀር በቤቷ ምንም ነገር የላትም” አለች።

3 ኤልሳዕም እንዲህ አላት፤ “እንግዲያው ሂጂና ከጎረቤቶችሽ ሁሉ ጥቂት ሳይሆን ብዙ ማድጋ ተዋሺ፤

4 ገብተሽም መዝጊያውን ባንቺና በልጆችሽ ላይ የኋሊት ዝጊው፤ ዘይቱንም በማድጋዎቹ ሁሉ ጨምሪ፤ እያንዳንዱ ማድጋ ሲሞላም ወደ አንድ በኩል አኑሪው።”

5 ስለዚህ ትታው ሄዳ መዝጊያውን በራሷና በልጆቿ ላይ የኋሊት ዘጋችው። ማድጎቹን እያቀረቡላትም እርሷ ትሞላ ጀመር።

6 ማድጋዎቹ ሁሉ ከሞሉ በኋላ ልጇን፣ “ሌላ ማድጋ አምጣ” አለችው።እርሱ ግን፣ “ምንም የቀረ ማድጋ የለም” ሲል መለሰላት። ከዚያም ዘይቱ መውረዱን አቆመ።

7 እርሷም ሄዳ ይህንኑ ለእግዚአብሔር ሰው ነገረችው። እርሱም፣ “ሄደሽ ዘይቱን በመሸጥ ዕዳሽን ክፈይ፤ የተረፈውም ለአንቺና ለልጆችሽ መተዳደሪያ ይሁን” አላት።

8 አንድ ቀን ኤልሳዕ ወደ ሱነም ሄደ። በዚያም አንዲት ሀብታም ሴት ነበረች፤ እርስዋም ምግብ እንዲበላ አጥብቃ ለመነችው፤ በዚያም ባለፈ ቍጥር ምግብ ለመብላት ወደ ቤቷ ይገባ ነበር።