2 ነገሥት 4:37-43 NASV

37 እርሷም ገብታ በእግሩ ላይ ወደቀች፤ በምድርም ላይ ተደፋች፤ ልጇንም ይዛ ወጣች።

38 ኤልሳዕ ወደ ጌልገላ ተመለሰ፤ በዚያም አገር ራብ ነበረ። የነቢያት ማኅበር በፊቱ ተቀምጠው ሳለ አገልጋዩን፣ “ትልቁን ምንቸት ጣድና ለእነዚህ ሰዎች ወጥ ሥራላቸው” አለው።

39 ከእነርሱም አንዱ ቅጠላ ቅጠል ለማምጣት ወደ ሜዳ ወጥቶ፤ ዱር በቀል ሐረግ አገኘ፤ ከሐረጉም ላይ የቅል ፍሬ ለቅሞ በልብሱ ሙሉ ይዞ ተመለሰና ቈራርጦ በወጡ ምንቸት ውስጥ ጨመረው፤ ምን እንደሆን ግን ማንም አላወቀም።

40 ሰዎቹ እንዲመገቡትም ወጡ ወጣ፤ ገና አንደ ቀመሱትም፣ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፤ በምንቸቱ ውስጥ የሚገድል መርዝ አለ!” ብለው ጮኹ፤ ሊመገቡትም አልቻሉም።

41 ኤልሳዕም፣ “እስቲ ዱቄት አምጡልኝ” አለ። ያንንም በምንቸቱ ውስጥ ጨምሮ፣ “እንዲመገቡት ለሰዎቹ አቅርቡላቸው” አለ። በምንቸቱም ውስጥ ጒዳት የሚያስከትል ነገር አልተገኘም።

42 አንድ ሰው ከበኵራቱ ፍሬ የተጋገረ ሃያ የገብስ ሙልሙልና ጥቂት የእሸት ዛላዎች በአቊማዳ ይዞ ከበኣልሻሊሻ ወደ እግዚአብሔር ሰው መጣ። ኤልሳዕም አገልጋዩን፣ “ሰዎቹ እንዲበሉት ስጣቸው” አለው።

43 አገልጋዩም፣ “ይህን እንዴት አድርጌ ለመቶ ሰው አቀርባለሁ?” ሲል ጠየቀ፤ኤልሳዕ ግን፣ “እንዲበሉት ለሰዎቹ ስጣቸው፤ እግዚአብሔር፣ ‘በልተው ይተርፋቸዋል’ ይላልና” አለው።