2 ነገሥት 5:5-11 NASV

5 የሶርያም ንጉሥ፣ “በል እንግዲያው አሁኑኑ ሂድ፤ እኔም ለእስራኤል ንጉሥ ደብዳቤ እጽፋለሁ” አለው፤ ስለዚህ ንዕማን ዐሥር መክሊት ብር፣ ስድስት ሺህ ሰቅል ወርቅና ዐሥር ሙሉ ልብስ ይዞ ሄደ።

6 ለእስራኤልም ንጉሥ የያዘው ደብዳቤ፣ “ከለምጹ እንድትፈውሰው ይህን ደብዳቤ አስይዤ አገልጋዬን ንዕማንን ወዳንተ ልኬዋለሁ” የሚል ነው።

7 የእስራኤልም ንጉሥ ደብዳቤውን ወዲያው እንዳነበበ ልብሱን ቀዶ፣ “ለምጽ እንድ ፈውሰው ይህን ሰው ወደ እኔ መላኩ እኔ ገድዬ ማዳን የምችል አምላክ ሆኜ ነውን? እንግዲህ ጠብ ሲፈልገኝ እዩ!” አለ።

8 የእግዚአብሔር ሰው ኤልሳዕ፣ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን መቅደዱን በሰማ ጊዜ እንዲህ ሲል ላከበት፤ “ልብስህን ለምን ቀደድህ? ሰውየው ወደ እኔ ይምጣ፤ ከዚያም በእስራኤል ነቢይ መኖሩን ያውቃል።”

9 ስለዚህ ንዕማን በፈረሶቹና በሠረገሎቹ ሆኖ በኤልሳዕ ቤት ደጃፍ ሲደርስ ቆመ።

10 ኤልሳዕም፣ “ሂድና በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ታጠብ፤ ሥጋህ ይፈወሳል፤ አንተም ትነጻለህ” ብሎ እንዲነግረው መልእክተኛ ላከበት።

11 ንዕማን ግን ተቈጥቶ እንዲህ በማለት ሄደ፤ ‘እኔ እኮ በርግጥ ወደ እኔ መጥቶ በመቆም የአምላኩን የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ፣ በእጁም ዳሶ ከለምጽ በሽታዬ የሚፈውሰኝ መስሎኝ ነበር።