2 ነገሥት 6:15-21 NASV

15 የእግዚአብሔር ሰው አገልጋይ በማለዳ ተነሥቶ ወደ ውጭ ሲወጣ፣ በፈረሶችና በሠረገሎች የተጠናከረ ሰራዊት ከተማዪቱን ከቧት ነበር። አገልጋዩም “ጌታዬ ሆይ፤ ምን ማድረግ ይሻለናል?” ሲል ጠየቀ።

16 ነቢዩም፣ “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ” አለው።

17 ኤልሳዕም፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ያይ ዘንድ እባክህ ዐይኖቹን ክፈትለት” ብሎ ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የአገልጋዩን ዐይኖች ከፈተለት፤ ሲመለከትም፤ የእሳት ፈረሶችና ሠረገሎች በኤልሳዕ ዙሪያ ተራራውን ሞልተውት አየ።

18 ሶርያውያንም ወርደው ወደ እርሱ ሲመጡ ኤልሳዕ፣ “ይህን ሕዝብ ዕውር አድርገው” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ስለዚህ ኤልሳዕ በጠየቀው መሠረት እግዚአብሔር ዕውር አደረጋቸው።

19 ኤልሳዕም፣ “መንገዱ በዚህ አይደለም፤ ከተማዪቱም ይህች አይደለችም፤ ወደምት ፈልጉት ሰው መርቼ እንዳደርሳችሁም እኔን ተከተሉኝ” አላቸው። ከዚያም መርቶ ወደ ሰማርያ ወሰዳቸው።

20 ወደ ከተማዪቱም ከገቡ በኋላ ኤልሳዕ፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዲያዩ የእነዚህን ሰዎች ዐይን ክፈት” አለ። እግዚአብሔርም ዐይኖቻቸውን ከፈተ። እነርሱም በሰማርያ ውስጥ መሆናቸውን አዩ።

21 የእስራኤልም ንጉሥ ባያቸው ጊዜ፣ “አባቴ ሆይ፤ ልግደላቸውን? ልፍጃቸውን?” ብሎ ኤልሳዕን ጠየቀው።