2 ነገሥት 6:18-24 NASV

18 ሶርያውያንም ወርደው ወደ እርሱ ሲመጡ ኤልሳዕ፣ “ይህን ሕዝብ ዕውር አድርገው” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ስለዚህ ኤልሳዕ በጠየቀው መሠረት እግዚአብሔር ዕውር አደረጋቸው።

19 ኤልሳዕም፣ “መንገዱ በዚህ አይደለም፤ ከተማዪቱም ይህች አይደለችም፤ ወደምት ፈልጉት ሰው መርቼ እንዳደርሳችሁም እኔን ተከተሉኝ” አላቸው። ከዚያም መርቶ ወደ ሰማርያ ወሰዳቸው።

20 ወደ ከተማዪቱም ከገቡ በኋላ ኤልሳዕ፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዲያዩ የእነዚህን ሰዎች ዐይን ክፈት” አለ። እግዚአብሔርም ዐይኖቻቸውን ከፈተ። እነርሱም በሰማርያ ውስጥ መሆናቸውን አዩ።

21 የእስራኤልም ንጉሥ ባያቸው ጊዜ፣ “አባቴ ሆይ፤ ልግደላቸውን? ልፍጃቸውን?” ብሎ ኤልሳዕን ጠየቀው።

22 እርሱም፣ “አትግደላቸው፤ ለመሆኑ በሰይፍህና በቀስትህ የማረክሃቸውን ትገድላቸው ዘንድ ይገባሃልን? አሁንም የሚበሉትንና የሚጠጡትን አስቀርብላቸው፤ በልተው ጠጥተውም ወደ ጌታቸውም ይሂዱ” አለው።

23 ስለዚህ ታላቅ ግብዣ አዘጋጅቶላቸው ከበሉና ከጠጡ በኋላ አሰናብቶአቸው ወደ ጌታቸው ሄዱ። የሶርያ አደጋ ጣዮችም የእስራኤልን ምድር ለመውረር ከዚያ በኋላ አልተመለሱም።

24 ከጥቂት ጊዜ በኋላም የሶርያ ንጉሥ ቤን ሐዳድ ሰራዊቱን ሁሉ ሰበሰበ፤ ወጥቶም ሰማርያን ከበባት።