2 ንጉሡ በክንዱ ላይ የተደገፈውም የጦር አለቃ፣ የእግዚአብሔርን ሰው፣ “እንዲያው ለመሆኑ፣ እግዚአብሔር የሰማያትን መስኮቶች ቢከፍት እንኳ ይህ ሊሆን ይችላልን?” ሲል ጠየቀው።ኤልሳዕም፣ “ይህን አንተው ራስህ በዐይንህ ታየዋለህ፤ ይሁን እንጂ ከዚያ አንዳች አትቀምስም” አለው።
3 በዚህ ጊዜ የሚያሠቅቅ የቆዳ በሽታ የያዛቸው አራት ሰዎች በከተማዪቱ መግቢያ በር አጠገብ ነበሩ፤ እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “እስክንሞት ድረስ በዚህ የምንቆየው ለምንድን ነው?
4 ታዲያ፣ ‘ወደ ከተማዪቱ እንግባ ብንል’ በዚያም ራብ ስላለ እንሞታለን፤ በዚሁም ብንሆን ያው መሞታችን እንደሁ አልቀረም፤ ስለዚህ ወደ ሶርያውያኑ ሰፈር ዝም ብለን እንሂድ፤ ዝም ካሉን ሕይወታችን ትተርፋለች፤ ከገደሉንም ያው ሞቶ መገላገል ነው።”
5 ከዚያም መሸትሸት ሲል ተነሥተው ወደ ሶርያውያን ሰፈር ሄዱ፤ ወደ ሰፈሩ ጥግ ሲደርሱም አንድም ሰው በዚያ አልነበረም።
6 ይህ የሆነበትም ምክንያት እግዚአብሔር የሠረገሎችንና የፈረሶችን እንዲሁም የብዙ ሰራዊት ድምፅ ሶርያውያን እንዲሰሙ አድርጎ ስለ ነበር ነው፤ እርስ በእርሳቸው፣ “እነሆ፣ የእስራኤል ንጉሥ በእኛ ላይ አደጋ ለመጣል፣ የኬጢያውያንንና የግብፃውያንን ነገሥታት ቀጥሮ አምጥቶብናል” ተባባሉ።
7 ከዚያም መሸትሸት ሲል ተነሥተው ሸሹ፤ ድንኳኖቻቸውን፣ ፈረሶቻቸውንና አህዮቻቸውንም አልወሰዱም ነፍሳቸውን ብቻ ለማዳን ሲሉ ሰፈሩን እንዲሁ እንዳለ ትተው ሄዱ።
8 ለምጽ ያለባቸውም ሰዎች ወደ ሰፈሩ አጠገብ ከደረሱ በኋላ፣ ከድንኳኖቹ ወደ አንዱ ገብተው በሉ፤ ጠጡም፤ ከዚያም ብር፣ ወርቅና ልብስ ይዘው በመሄድ ደበቁት። ተመልሰው በመምጣትም ወደ ሌላው ድንኳን ገብተው ሌሎች ነገሮችን በመውሰድ እንደዚሁ ደበቁ።