2 ነገሥት 9:3-9 NASV

3 ከዚያም ማሰሮውን ይዘህ ዘይቱን በራሱ ላይ አፍስስና፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ እኔ በእስራኤል ላይ እንድትነግሥ ቀባሁህ” ’ ብለህ ዐውጅ። ከዚያም በሩን ከፍተህ ሩጥ፤ ፈጽሞ አትዘግይ።”

4 ስለዚህ ጐልማሳው ነቢይ በሬማት ወደምትገኘው ገለዓድ ሄደ።

5 በዚያ እንደ ደረሰም፣ የሰራዊቱ ጦር መኰንኖች በአንድነት ተቀምጠው ነበር፤ እርሱም “መኰንን ሆይ፤ ወደ አንተ ተልኬአለሁ” አለ።ኢዩም፣ “ለማንኛችን ነው?” ሲል ጠየቀ።እርሱም፣ “መኰንን ሆይ፤ ለአንተ ነው” ብሎ መለሰ።

6 ኢዩም ተነሥቶ ወደ ቤት ገባ፤ ከዚያም ነቢዩ ዘይቱን በኢዩ ላይ አፈሰሰና እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ እንድትነግሥ ቀብቼሃለሁ።

7 የአገልጋዮቼን የነቢያትን ደም እንዲሁም የእግዚአብሔርን አገልጋዮች ደም ሁሉ ከኤልዛቤል እጅ እበቀል ዘንድ አንተ የጌታህን የአክዓብን ቤት ትመታለህ።

8 የአክዓብ ቤት በሙሉ ይጠፋል፤ ባሪያም ይሁን ተወላጅ፣ በእስራኤል የሚገኘውን የመጨረሻ ወንድ ልጅ ሁሉ ከአክዓብ እቈርጣለሁ።

9 ከእንግዲህ የአክዓብን ቤት፣ እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት፣ እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ።