7 የአገልጋዮቼን የነቢያትን ደም እንዲሁም የእግዚአብሔርን አገልጋዮች ደም ሁሉ ከኤልዛቤል እጅ እበቀል ዘንድ አንተ የጌታህን የአክዓብን ቤት ትመታለህ።
8 የአክዓብ ቤት በሙሉ ይጠፋል፤ ባሪያም ይሁን ተወላጅ፣ በእስራኤል የሚገኘውን የመጨረሻ ወንድ ልጅ ሁሉ ከአክዓብ እቈርጣለሁ።
9 ከእንግዲህ የአክዓብን ቤት፣ እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት፣ እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ።
10 ኤልዛቤልን ግን በኢይዝራኤል ዕርሻ ውሾች ይበሏታል፤ የሚቀብራትም አይኖርም።’ ” ይህን ተናግሮም መዝጊያውን ከፍቶ ሮጠ።
11 ኢዩ ወጥቶ የጦር አለቆች ወደሆኑት ጓደኞቹ እንደ ደረሰ፣ ከመካከላቸው አንዱ “ሁሉም ነገር ሰላም ነው? ይህ እብድ ወደ አንተ የመጣው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።ኢዩም “ሰውየውንም ሆነ የሚናገረውን እናንተም ታውቃላችሁ” ሲል መለሰ።
12 እነርሱም፣ “ይህማ ትክክል አይደለም ይልቅስ እውነቱን ንገረን” አሉት።ኢዩም እንዲህ አለ፤ “እርሱ የነገረኝማ ይህ ነው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የእስራኤል ንጉሥ እንድትሆን ቀብቼሃለሁ።’ ”
13 ከዚያ ሁሉም ቶሎ ብለው ልብሳቸውን እያወለቁ በሚራመድበት ደረጃ ላይ አነጠፉ፤ ከዚያም መለከት ነፍተው፣ “ኢዩ ነግሦአል” አሉ።