2 ዜና መዋዕል 1:11-17 NASV

11 እግዚአብሔርም ሰሎሞንን እንዲህ አለው፤ “የልብህ መሻት ይህ ስለ ሆነ፣ ብልጥግናና ሀብት ወይም የጠላቶችህን ነፍስ ወይም ረጅም ዕድሜ ስላልጠየቅህ፣ ነገር ግን ባነገሥሁህ ሕዝቤ ላይ የምትገዛበትን ጥበብና ዕውቀት ስለ ጠየቅህ፣

12 ጥበብና ዕውቀት ይሰጥሃል፤ እንዲሁም ከአንተ በፊት የነበረ ማንኛውም ንጉሥ ያላገኘውን፣ ከአንተ በኋላም የሚነሣው የማያገኘውን ብልጽግና፣ ሀብትና ክብር እሰጥሃለሁ።”

13 ሰሎሞንም የመገናኛው ድንኳን ካለበት ከገባዖን ኰረብታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፤ በእስራኤልም ላይ ነገሠ።

14 ሰሎሞን ሠረገሎችንና ፈረሶችን ሰበሰበ፤ እርሱም አንድ ሺህ አራት መቶ ሠረገሎችና ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሶች ነበሩት፤ እነርሱንም በሠረገላ ከተሞችና እርሱ ባለበት በኢየሩሳሌም ከተማ አኖራቸው።

15 ንጉሡም ወርቁና ብሩ በኢየሩሳሌም እንደ ተራ ድንጋይ እንዲበዛ፣ ዝግባውም በየኰረብታው ግርጌ እንደሚገኝ የሾላ ዛፍ እንዲበዛ አደረገ።

16 የሰሎሞንም ፈረሶች የመጡት ከግብፅና ከቀዌ ነበር፤ ከቀዌ የገዟቸውም የንጉሡ ነጋዴዎች ነበሩ።

17 ከግብፅ ያስገቧቸውም አንዱን ሠረገላ በስድስት መቶ ሰቅል ብር፣ አንዱን ፈረስ በአንድ መቶ አምሳ ሰቅል ብር ገዝተው ነው። እነዚህንም ደግሞ ለኬጢያዊያንና ለሦርያውያን ነገሥታት ሁሉ ይሸጡላቸው ነበር።