2 ዜና መዋዕል 2:8-14 NASV

8 ሰዎችህ ከሊባኖስ እንጨት በመቍረጥ ሥራ ዐዋቂዎች መሆናቸውን ስለማውቅ፣ ከሊባኖስ የዝግባ፣ የጥድና የሰንደል ዕንጨትም ላክልኝ፤ ሰዎቼም ከሰዎችህ ጋር አብረው ይሠራሉ።

9 የምሠራው ቤተ መቅደስ ትልቅና እጅግ ውብ መሆን ስላለበት፣ ብዙ ጠርብ ያዘጋጁልኛልና።

10 ዕንጨቱን ለሚቈርጡ አገልጋዮችህ ሃያ ሺህ የቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ ዱቄት፣ ሃያ ሺህ የባዶስ መስፈሪያ ወይን ጠጅና ሃያ ሺህ የባዶስ መስፈሪያ ዘይት እሰጣለሁ።”

11 የጢሮስ ንጉሥ ኪራምም ለሰሎሞን እንዲህ ሲል በደብዳቤ መለሰለት፤“እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለሚወድድ አንተን በእነርሱ ላይ አነገሠህ፤”

12 ኪራምም በመቀጠል እንዲህ አለ፤“ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ! ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስን፣ ለራሱም ቤተ መንግሥትን የሚሠራ፣ ብልኅነትንና ማስተዋልን የተሞላ ጥበበኛ ልጅ ለንጉሥ ዳዊት ሰጥቶአልና።

13 “እጅግ ብልሃተኛ የሆነውን ኪራም አቢን ልኬልሃለሁ፤

14 እርሱም እናቱ ከዳን ወገን፣ አባቱም የጢሮስ አገር ሰው ነው፤ በወርቅና በብር፣ በናስና በብረት፣ በድንጋይና በዕንጨት፤ እንዲሁም በሐምራዊና በሰማያዊ፣ በቀይ ግምጃና በቀጭን በፍታ ሥራ የሠለጠነ ሲሆን፣ በልዩ ልዩ ቅርጻ ቅርጽ ሥራ ልምድ ያካበተና የተሰጠውን ማናቸውንም ንድፍ በሥራ መተርጐም የሚችል ባለ ሙያ ነው። እርሱም ከአንተ የእጅ ሥራ ባለሙያዎችና ከጌታዬ ከአባትህ የእጅ ሥራ ባለ ሙያዎች ጋር አብሮ ይሠራል።