2 ዜና መዋዕል 20:26-32 NASV

26 በአራተኛውም ቀን እግዚአብሔርን ባመሰገኑበት በበረከት ሸለቆ ተሰበሰቡ፤ ያም ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የበረከት ሸለቆ ተብሎ የተጠራው ከዚህ የተነሣ ነው።

27 እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ እንዲደሰቱ ስላደረጋቸው፣ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሁሉ በኢዮሣፍጥ እየተመሩ፣ በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

28 ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ እንደ ገቡም በበገና፣ በመሰንቆና በመለከት ድምፅ ታጅበው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አመሩ።

29 እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች እንዴት እንደተዋጋቸው በሰሙ መንግሥታት ሁሉ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርሀት ወደቀባቸው።

30 አምላኩ በየአቅጣጫው ዕረፍት ስለ ሰጠው፣ የኢዮሣፍጥ መንግሥት ሰላም አግኝቶ ነበር።

31 ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ላይ ነገሠ። መንገሥ በጀመረ ጊዜም ዕድሜው ሠላሳ አምስት ዓመት ሲሆን፣ በኢየሩሳሌም ተቀሞጦ ሃያ አምስት ዓመት ገዛ። እናቱም የሺልሒ ልጅ ዓዙባ ነበረች።

32 እርሱም በአባቱ በአሳ መንገድ ሄደ፤ ከዚያም ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔርም ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ።