2 ዜና መዋዕል 23:6-12 NASV

6 ተረኛ ከሆኑት ካህናትና ሌዋውያን በቀር ማንም ሰው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አይግባ፤ እነርሱ የተቀደሱ ስለሆኑ ይግቡ፤ የቀሩት ሰዎች በሙሉ ግን፣ ወደ ቤተ መቅደሱ እንዳይገቡ እግዚአብሔር ያዘዘውን ይጠብቁ።

7 ሌዋውያኑም የጦር መሣሪያቸውን በእጃቸው ይዘው በንጉሡ ዙሪያ ይቁሙ፤ ወደ ቤተ መቅደሱ የሚገባ ማንኛውም ሰው ይገደል፤ ንጉሡ በሚሄድበትም ቦታ ሁሉ አብረውት ይሁኑ።”

8 ሌዋውያኑና ይሁዳ ሁሉ ልክ ካህኑ ዮዳሄ እንዳዘዘው አደረጉ፤ ካህኑ ዮዳሄ ከጥበቃ ክፍሎች የትኛውንም አላሰናበተም ነበርና፣ እያንዳንዱ በሰንበት ቀን በሥራ ላይ የሚሰማሩትንና ከሥራ የሚወጡትን የራሱን ሰዎች ወሰደ፤

9 ከዚያም በቤተ መቅደሱ የነበሩትን የንጉሥ ዳዊት ጦሮች፣ ታላላቅና ታናናሽ ጋሻዎች ለመቶ አለቆቹ ሰጣቸው።

10 ሰዎቹም ሁሉ እያንዳንዳቸው መሣሪያቸውን በእጃቸው እንደ ያዙ ከቤተ መቅደሱ ደቡብ አንሥቶ እስከ ሰሜን ድረስ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ አጠገብ በንጉሡ ዙሪያ እንዲቆሙ አደረገ።

11 ዮዳሄና ወንዶች ልጆቹ የንጉሡን ልጅ አምጥተው ዘውድ ጫኑለት፤ የኪዳኑንም መጽሐፍ ሰጥተውት አነገሡት፤ ቀብተውትም፣ “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!” እያሉ ጮኹ።

12 ጎቶልያም የሚሯሯጠውንና ደስታውን ለንጉሡ የሚገልጠውን ሕዝብ ሁካታ ስትሰማ፣ ሕዝቡ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሄደች።