15 በኢየሩሳሌምም፣ ንድፎቻቸው በባለ ሙያዎች የተዘጋጁ፣ በመጠበቂያ የግንብ ማማዎችና በየማዕዘኑ መከላከያዎች ላይ ፍላጻ የሚስፈነጠርባቸውንና ትልልቅ ድንጋዮች የሚወረወርባቸውን መሣሪያዎች አሠራ። እስኪበረታም ድረስ በሚያስደንቅ ሁኔታ ስለታገዘ፣ ዝናው በርቀትና በስፋት ተሰማ።
16 ዖዝያን ከበረታ በኋላ ግን ዕብሪቱ ለውድቀት ዳረገው። በዕጣን መሠዊያው ላይ ዕጣን ለማጠን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመግባቱ እግዚአብሔርን በደለ፤
17 ካህኑም ዓዛርያስ ቈራጥ ከሆኑ ከሌሎች ሰማንያ የእግዚአብሔር ካህናት ጋር ተከትሎት ገባ።
18 እነርሱም ፊት ለፊት በመጋፈጥ፣ “ዖዝያን ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ማጠን ለተለዩትና የአሮን ዘሮች ለሆኑት ለካህናቱ እንጂ ለአንተ የተገባ አይደለም፤ እግዚአብሔርን በድለሃልና ከመቅደሱ ውጣ፤ ከእግዚአብሔር አምላክ ዘንድም ክብር አይሆንልህምና” አሉት።
19 ጥና በእጁ ይዞ ዕጣን ለማጠን ዝግጁ የነበረው ዖዝያን ተቈጣ፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ በዕጣን መሠዊያው ፊት ሆኖ ካህናቱ ላይ እየተቈጣ ሳለ፣ በግንባሩ ላይ ለምጽ ወጣበት።
20 ሊቀ ካህናቱ ዓዛርያስና ሌሎቹ ካህናት ሁሉ በተመለከቱት ጊዜ፣ በግንባሩ ላይ ለምጽ እንደ ወጣበት አዩ። ስለዚህ አጣድፈው አስወጡት፤ በእርግጥ እርሱም ራሱ ለመውጣት ቸኵሎ ነበር፤ እግዚአብሔር አስጨንቆታልና።
21 ንጉሥ ዖዝያን እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ለምጻም ነበረ። ለምጻም በመሆኑም ከቤተ መቅደስ ተወግዶ ነበርና በተለየ ቤት ተቀመጠ። ከዚያም ልጁ ኢዮአታም የቤተ መንግሥቱን አስተዳደር በኀላፊነት ተረክቦ የአገሩን ሕዝብ ይመራ ጀመር።