ሚክያስ 1:2-8 NASV

2 እናንተ አሕዛብ ሆይ፤ ሁላችሁም ስሙ፤ምድር ሆይ፤ በውስጧም የምትኖሩ ሁሉ አድምጡ፤ጌታ ከቅዱስ መቅደሱ፣ልዑል እግዚአብሔር በእናንተ ላይ ይመሰክርባችኋል።

3 እነሆ፤ እግዚአብሔር ከመኖሪያ ስፍራው ይመጣል፤ወርዶም በምድር ከፍታዎች ላይ ይራመዳል።

4 ተራሮች ከሥሩ ይቀልጣሉ፤ሸለቆዎችም ይሰነጠቃሉ፤በእሳት ፊት እንዳለ ሰም፣በገደል ላይ እንደሚወርድ ፈሳሽ ይሆናሉ።

5 ይህ ሁሉ የሚሆነው ስለ ያዕቆብ በደል፣ስለ እስራኤልም ቤት ኀጢአት ነው።የያዕቆብ በደል ምንድን ነው?ሰማርያ አይደለችምን?የይሁዳስ የኰረብታ መስገጃ ምንድን ነው?ኢየሩሳሌም አይደለችምን?

6 “ስለዚህ ሰማርያን የፍርስራሽ ክምር፣ወይን የሚተከልባትም ስፍራ አደርጋታለሁ፤ድንጋዮቿን ወደ ሸለቆ አወርዳለሁ፤መሠረቷንም ባዶ አደርጋለሁ።

7 ጣዖቶችዋ ሁሉ ይሰባበራሉ፤ለቤተ መቅደሷ የቀረበው ገጸ በረከት በእሳት ይቃጠላል፤ምስሎችዋን ሁሉ እደመስሳለሁ፤ገጸ በረከቷን በዝሙት አዳሪነት እንደ ሰበሰበች ሁሉ፣አሁንም ገጸ በረከትዋ የዝሙት አዳሪነት ዋጋ መቀበያ ይሆናል።

8 በዚህ ምክንያት አለቅሳለሁ፤ ዋይ ዋይም እላለሁ፤ባዶ እግሬንና ዕርቃኔን እሄዳለሁ፤እንደ ቀበሮ አላዝናለሁ፤እንደ ጒጒትም አቃስታለሁ።