11 ሕፃን እንኳ ጠባዩ ንጹሕና ቅን መሆኑ፣ከአድራጎቱ ይታወቃል።
12 የሚሰሙ ጆሮዎች፣ የሚያዩ ዐይኖች፣ሁለቱንም እግዚአብሔር ሠርቷቸዋል።
13 እንቅልፍ አትውደድ፤ አለዚያ ድኻ ትሆናለህ፤ዐይንህን ክፈት፤ የተትረፈረፈ ምግብ ይኖርሃል።
14 ዕቃ የሚገዛ፣ “የማይረባ ነው፤ የማይረባ ነው” ብሎ ያራክሳል፤ሲመለስ ግን በግዢው ይኵራራል።
15 ወርቁም አለ፤ ቀዩም ዕንቊ ተትረፍርፎአል፤ዕውቀት የሚናገሩ ከንፈሮች ግን ብርቅ ጌጦች ናቸው።
16 ለማይታወቅ ሰው ዋስ የሆነውን ልብሱን ግፈፈው፤ለዘልዛላ ሴት የተዋሰውን በቃሉ ያዘው።
17 ሰው በማጭበርበር ያገኘው ምግብ ይጣፍጠዋል፤በመጨረሻ ግን አፉን ኰረት ሞልቶት ያገኘዋል።