ሰቆቃወ 2:16-21 NASV

16 ጠላቶችሽ ሁሉ በአንድ ላይ፣አፋቸውን በኀይል ከፈቱ፤ጥርሳቸውን እያፏጩ አሾፉ፤እንዲህም አሉ፤ “ውጠናታል፤የናፈቅነው ጊዜ ይህ ነበር፤ኖረንም ልናየው በቃን።”

17 እግዚአብሔር ያሰበውን አደረገ፤ከረዥም ጊዜ በፊት የተናገረውን፣ቃሉን ፈጸመ፤ያለ ርኅራኄ አፈረሰሽ፤ጠላት በሥቃይሽ ላይ እንዲደሰት፣የጠላትሽንም ቀንድ ከፍ ከፍ አደረገ።

18 የሕዝቡ ልብ፣ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።የጽዮን ሴት ልጅ ቅጥር ሆይ፤ቀንና ሌሊት፣እንባሽ እንደ ወንዝ ይፍሰስ፤ለራስሽ ዕረፍትን አትስጪ፣ዐይኖችሽ ከማንባት አያቋርጡ።

19 የሌሊቱ ሰዓት ሲጀምር፣ተነሺ በሌሊት ጩኺ፤በእግዚአብሔር ፊት፣ልብሽን እንደ ውሃ አፍስሺ፤በየመንገዱ ዳር ላይ፣ በራብ ስለወደቁት፣ስለ ልጆችሽ ሕይወት፣ እጆችሽን ወደ እርሱ አንሺ።

20 አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ እይ፤ ተመልከትም፤በማን ላይ እንዲህ አድርገህ ታውቃለህ?በውኑ እናቶች ሕፃኖቻቸውን፣ተንከባክበው ያሳደጓቸውን ልጆች ይብሉን?ካህኑና ነቢዩስ፣በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ይገደሉን?

21 በየመንገዱ ዐቧራ ላይ፣ወጣትና ሽማግሌ በአንድነት ወደቁ፤ወይዛዝርቴና ጐበዛዝቴ፣በሰይፍ ተገደሉ፤በቍጣህ ቀን ገደልሃቸው፤ያለ ርኅራኄም ዐረድሃቸው።