ነህምያ
ምዕራፎች 2:1-7
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም
1በንጉሡ በአርጤክስስ ዘመነ መንግሥት በሃያኛው ዓመት ኒሳን ተብሎ በሚጠራው ወር የወይን ጠጅ በመጣለት ጊዜ፣ የወይን ጠጁን አንሥቼ ለንጉሡ ሰጠሁት። ቀድሞ በፊቱ ዐዝኜ አላውቅም ነበር፤
2ስለዚህ ንጉሡ፣ “ሳትታመም ፊትህ ለምን እንዲህ ዐዘነ? መቼም ይህ የልብ ሐዘን እንጂ ሌላ አይደለም” አለኝ።እኔም በጣም ፈርቼ ነበር፤
3ለንጉሡም “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር፤ አባቶቼ የተቀበሩባት ከተማ ስትፈርስ፣ በሮቿም በእሳት ሲቃጠሉ ለምን ፊቴ አይዘን?” አልሁት።
4ንጉሡም፣ “ታዲያ ምን ትፈልጋለህ?” አለኝ። ከዚያም ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይሁ፤
5ለንጉሡም፣ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ቢሆንና ባሪያህ በፊትህ ሞገስ ቢያገኝ፣ እንደ ገና እንድሠራት አባቶቼ ወደ ተቀበሩባት ወደ ይሁዳ ከተማ እንድሄድ ይፈቀድልኝ” አልሁት።
6ከዚያም ንጉሡ አጠገቡ ከተቀመጠችው ንግሥት ጋር በመሆን፣ “ጒዞህ ምን ያህል ቀን ይፈጃል? መቼስ ትመለሳለህ?” ሲል ጠየቀኝ። ንጉሡም እኔን ለመስደድ ደስ አለው፤ እኔም ጊዜውን ወሰንሁ።
7ደግሞም እንዲህ አልሁት፤ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ቢሆን፣ ይሁዳ እስክደርስ ድረስ በደኅና እንዲያሳልፉኝ ከኤፍራጥስ ማዶ ላሉት አገረ ገዦች ደብዳቤ ይሰጠኝ፤