ኢያሱ 11:16-22 NASV

16 ኢያሱ ያንን ምድር በሙሉ ማለት ተራራማውን አገር፣ ኔጌቭን ሁሉ፣ የጎሶምን ምድር በሙሉ፣ የምዕራቡን ቈላ፣ ዓረባን እንዲሁም የእስራኤልን አገር ደጋውንና ቈላውን ጠቅልሎ ያዘ፤

17 እንዲሁም እስከ ሴይር በሚደርሰው ከሐላቅ ተራራ አንሥቶ ከአርሞንዔም ተራራ በታች በሊባኖስ ሸለቆ ውስጥ እስካለው እስከ በኣልጋድ ድረስ ያለውን ምድር በሙሉ ያዘ፤ ነገሥታታቸውንም ሁሉ ያዘ፤ መትቶም ገደላቸው።

18 ኢያሱ ከእነዚህ ነገሥታት ጋር ብዙ ዘመን የፈጀ ጦርነት አደረገ።

19 በገባዖን ከሚኖሩ ከኤዊያውያን በስተቀር፣ ከእስራኤላውያን ጋር የሰላም ውል ያደረገ አንድም ከተማ አልነበረም፤ ሁሉንም የያዙት በጦርነት ነው።

20 እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት፣ ያለ አንዳች ርኅራኄ ፈጽሞ ይደመስሳቸው ዘንድ እስራኤልን እንዲወጉ ልባቸውን ያደነደነው ራሱ እግዚአብሔር ነውና።

21 በዚያን ጊዜ ኢያሱ ሄዶ በተራራማው አገር ማለት በኬብሮን፣ በዳቤርና በአናብ እንዲሁም በመላው የይሁዳና የእስራኤል ተራራማ አገሮች ያሉትን የዔናቅን ዘሮች ከነከተሞቻቸው በሙሉ ደመሰሳቸው፤

22 ከእነዚህም ጥቂቶቹ ብቻ በጋዛ፣ በጌትና በአሽዶድ ሲቀሩ፣ በእስራኤል የቀሩ የዔናቅ ዘሮች ግን አልነበሩም።