ኢያሱ 13 NASV

ወደ ፊት የሚያዝ ምድር

1 ኢያሱ በሸመገለና ዕድሜው በገፋ ጊዜ፣ እግዚአብሔር እንዲህ አለው፤ “እነሆ አርጅተሃል፤ ዕድሜህም ገፍቶአል፤ ነገር ግን መያዝ ያለበት እጅግ በጣም ሰፊ ምድር ገና አለ።

2 “የሚቀረውም ምድር ይህ ነው፤ እርሱም የፍልስጥኤማውያንና የጌሹራውያን አገር ሁሉ ነው፤

3 ከግብፅ በስተ ምሥራቅ ከሚገኘው ከሺሖር ወንዝ አንሥቶ፣ በሰሜን እስከ አቃሮን ወሰን ያለው አገር፣ ሁሉም እንደ ከነዓናውያን ምድር ይቈጠራል፤ ይኸውም በጋዛ፣ በአሽዶድ፣ በአስቀሎና፣ በጌትና በአቃሮን የሚኖሩትን የአምስቱን የፍልስጥኤማውያን ገዦች ምድር የሚያካትት ሲሆን፣ ይህም የኤዋውያን ምድር ነበር።

4 በደቡብ በኩል የከነዓናውያን ምድር ሁሉና የሲዶናውያን ይዞታ ከሆነችው ከመዓራ አንሥቶ እስከ አፌቅ ያለው የአሞራውያን ግዛት፣

5 የጌባላውያንም ምድር፤ በምሥራቅም ከበኣልጋድ አንሥቶ በአርሞንዔም ተራራ ግርጌ አልፎ፣ እስከ ሐማት መተላለፊያ ያለው የሊባኖስ ምድር ሁሉ ነው።

6 “ከሊባኖስ እስከ ማሴሮን ባለው ተራራማ ምድር ላይ የሚኖሩትን ሁሉ፣ ሲዶናውያንንም ጭምር እኔው ራሴ ከእስራኤላውያን ፊት አሳድጄ አስወጣቸዋለሁ። ብቻ አንተ ባዘዝሁህ መሠረት ምድሪቱን ርስት አድርገህ ለእስራኤላውያን አካፍል።

7 ይህንንም ለዘጠኙ ነገድና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገህ አካፍል።”

ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለው ምድር አከፋፈል

8 ሌላው የምናሴ ነገድ እኩሌታ፣ የሮቤል ነገድና የጋድ ነገድ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ እንደየ ድርሻቸው ከፋፍሎ በመደበላቸው መሠረት፣ ራሱ ሙሴ የሰጣቸውን ርስት ተቀበሉ።

9 ይህም ከአርኖን ሸለቆ ዳርቻ ካለው ከአሮዔርና በሸለቆው መካከል ካለችው ከተማ አንሥቶ እስከ ዲቦን የሚደርሰውን የሜድባን ደጋማ ምድር በሙሉ ይይዛል፤

10 እንዲሁም በሐሴቦን ተቀምጦ እስከ አሞናውያን ዳርቻ የገዛውን የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ከተሞች ሁሉ ያጠቃልላል፤

11 በተጨማሪም ገለዓድን፣ የጌሹራውያንንና የማዕካታውያንን ግዛት ሁሉ፣ የአርሞንዔምን ተራራ በሙሉ፣ ባሳንንም ሁሉ እስከ ሰልካ ድረስ ይይዛል፤

12 ይህም በአስታሮትና በኤድራይ ሆኖ የገዛውን በባሳን ያለውን የዐግን መንግሥት በሙሉ ያጠቃልላል፤ ዐግም በሕይወት ከቀሩት ከመጨረሻዎቹ ከራፋይም ዘሮች አንዱ ነበር፤ እነዚህንም ሙሴ ድል አደረጋቸው፤ ምድራቸውንም ያዘ፤

13 ነገር ግን እስራኤላውያን የጌሹርንና የማዕካትን ሕዝብ ስላላስወጡ፣ እስከ ዛሬ ድረስ በመካከላቸው ይኖራሉ።

14 ለሌዊ ነገድ ግን ርስት አልሰጠም፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርበው ቊርባን፣ በተሰጣቸው ተስፋ መሠረት ርስታቸው ነውና።

15 ሙሴ በየጐሣቸው መድቦ ለሮቤል ነገድ የሰጠው ርስት ይህ ነው፤

16 ድንበራቸው ከአርኖን ሸለቆ ዳርቻ ካለው ከአሮዔርና ከሸለቆው መካከል ካለችው ከተማ አንሥቶ ያለው ግዛት ሲሆን፣ ሜድባ አጠገብ ያለውን ደጋውን አገር በሙሉ፣

17 ሐሴቦንና በደጋው ላይ ያሉትን ከተሞችዋን በሙሉ፣ እንዲሁም ዲቦንን፣ ባሞትባኣልን፣ ቤትበኣልምዖን፣

18 ያሀጽን፣ ቅዴሞትን፣ ሜፍዓትን፣

19 ቂርያታያምን፣ ሴባማን፣ በሸለቆው ኰረብታ ላይ ያለችውን ጼሬትሻሐርን፣

20 ቤተፌጎርን፣ የፈስጋን ሸንተረሮችና ቤትየሺሞትን፣

21 ማለት በደጋው አገር የሚገኙት ከተሞች ሁሉና መቀመጫውን በሐሴቦን አድርጎ የገዛውን የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት በሙሉ ያካትታል። ሙሴ ሴዎንንና በዚያው ምድር ተቀማጭ የነበሩትን መሳፍንት፤ አዊ፣ ሮቆም፣ ሱር፣ ሑርና ሪባ የተባሉትን የምድያም አለቆች ድል አደረጋቸው።

22 በጦር ሜዳ ከሞቱት ሌላ እስራኤላውያን የቢዖርን ልጅ ምዋርተኛውን በለዓምን በሰይፍ መትተው ገደሉት።

23 የሮቤል ነገድ ወሰን የዮርዳኖስ ወንዝ ነው፤ የሮቤል ነገድ በየጐሣቸው የወረሷቸው ከተሞችና መንደሮቻቸው እነዚህ ነበሩ፤

24 ሙሴ በየጐሣቸው መድቦ ለጋድ ነገድ የሰጠው ርስት ይህ ነው፤

25 ድንበራቸው ኢያዜር፣ የገለዓድን ከተሞች በሙሉ በረባት አጠገብ እስካለው እስከ አሮዔር የሚደርሰውን የአሞናውያን አገር እኩሌታ፣

26 ከሐሴቦን እስከ ራማት ምጽጴና ከዚያም እስከ ብጦኒም፣ ከመሃናይም እስከ ደቤር ግዛት ያለውን፣

27 በሸለቆው ውስጥ ደግሞ ቤትሀራምን፣ ቤትኒምራን፣ ሱኮትን፣ ዳፎንንና እስከ ኪኔሬት ባሕር ጫፍ የሚደርሰውን ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን ቀሪውን የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት ያካትታል፤

28 የጋድ ነገድ በየጐሣቸው የወረሷቸው ከተሞችና መንደሮቻቸው እነዚህ ነበሩ።

29 ሙሴ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ማለት ለገሚሱ የምናሴ ቤተ ሰብ ዘሮች በየጐሣቸው የሰጣቸው ርስት ይህ ነው፤

30 ድንበራቸው ከመሃናይም አንሥቶ ባሳንን በሙሉ ይጨምርና፣ በባሳን ያሉትን ሥልሳ የኢያዕር ከተሞች ሁሉ ይዞ የባሳን ንጉሥ የዐግን ግዛት ሁሉ የሚያካትት ሲሆን፣

31 የገለዓድን እኩሌታ፣ በባሳን የዐግ መንግሥት ዋና ከተማ የሆኑትን አስታሮትንና ኤድራይን ይጨምራል፤ እነዚህ ለምናሴ ልጅ ለማኪር ዘሮች የተሰጡ ሲሆን፣ ይህም ለግማሾቹ የማኪር ልጆች በየጐሣቸው የተሰጡ ናቸው።

32 ሙሴ ከኢያሪኮ በስተ ምሥራቅ፣ ከዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ሜዳ ሳለ የሰጣቸው ርስት ይህ ነበር።

33 ለሌዊ ነገድ ግን ሙሴ ርስት አልሰጠም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንደ ተናገራቸው እርሱ ራሱ ርስታቸው ነውና።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24