ኢያሱ 19 NASV

ለስምዖን ነገድ የተመደበው ድርሻ

1 ሁለተኛው ዕጣ ለስምዖን ነገድ በየጐሣ በየጐሣው ወጣ፤ ርስታቸውም ዙሪያውን በይሁዳ ነገድ ርስት የተከበበ ነበር፤

2 ይህም የሚከተሉትን ያካትታል፤ ቤርሳቤህ፣ ሤባ፣ ሞላዳ፣

3 ሐጸር ሹዓል፣ ባላ፣ ዔጼም፣

4 ኤልቶላድ፣ በቱል፣ ሔርማ፣

5 ጺቅላግ፣ ቤትማርካቦት፣ ሐጸርሱሳ፣

6 ቤተለባኦትና ሻሩሔን ነበሩ፤ እነዚህ ዐሥራ ሦስት ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው።

7 ዓይን፣ ሪሞን፣ ዔቴርና ዓሻን የተባሉት አራት ከተሞቻቸውና መንደሮቻቸው፣

8 ደግሞም እስከ ባዕላትብኤር ወይም ኔጌብ ውስጥ እስካለው እስከ ራማት ድረስ ባሉት ከተሞች ዙሪያ የሚገኙት መንደሮች ሁሉ ከእነዚሁ ጋር ይጠቃለላሉ።እንግዲህ በየጐሣው የተደለደለው የስምዖን ነገድ ርስት ይህ ነበር።

9 የይሁዳ ነገድ የያዘው ርስት እጅግ ሰፊ ስለ ነበር፣ ከይሁዳ ነገድ ድርሻ ተከፍሎ ለስምዖን ነገድ በርስትነት ተሰጠ፤ ከዚህ የተነሣም የስምዖን ነገድ በይሁዳ ነገድ ድርሻ ርስት ሊካፈል ቻለ።

ለዛብሎን ነገድ የተመደበው ድርሻ

10 ሦስተኛው ዕጣ ለዛብሎን ነገድ በየጐሣ በየጐሣው ወጣ፤የርስታቸውም ድንበር እስከ ሣሪድ ይደርሳል፤

11 ወደ ምዕራብም በመሄድ በመርዓላ በኩል ያልፋል፤ ደባሼትን ተጠግቶም በዮቅንዓም አጠገብ እስካለው ወንዝ ድረስ ይዘልቃል።

12 ከሣሪድም ወደ ምሥራቅ በመታጠፍ፣ የፀሓይ መውጫ ወደ ሆነው አገር ወደ ኪስሎትታቦር በመዝለቅ እስከ ዳብራት ሄዶ ወደ ያፊዓ ያቀናል፤

13 ከዚያም ወደ ምሥራቅ በመቀጠል፣ ወደ ጋትሔፍርና ወደ ዒትቃጺን ይዘልቃል፤ ከዚያ ደግሞ ወደ ሪሞን በመሄድ፣ ወደ ኒዓ ይታጠፋል።

14 በስተ ሰሜንም በኩል ወደ ሐናቶን ይዞርና በይፍታሕኤል ሸለቆ ላይ ይቆማል።

15 ደግሞም ቀጣትን፣ ነህላልን፣ ሺምሮንን፣ ይዳላንና ቤተ ልሔምን ይጨምራል፤ እነዚህም ከነ መንደሮቻቸው ዐሥራ ሁለት ከተሞች ናቸው።

16 እነዚህ ሁሉ ለዛብሎን ነገድ ርስት ሆነው ለየጐሣ ለየጐሣው የተደለደሉ ከተሞችና መንደሮቻቸው ነበሩ።

ለይሳኮር ነገድ የተመደበው ድርሻ

17 አራተኛው ዕጣ ለይሳኮር ነገድ በየጐሣ በየጐሣው ወጣ፤

18 ምድራቸውም የሚከተሉትን ያካትታል፤ኢይዝራኤል፣ ከስሎት፣ ሱነም፣

19 ሐፍራይም፣ ሺኦን፣ አናሐራት፣

20 ረቢት፣ ቂሶን፣ አቤጽ፣

21 ሬሜት፣ ዐይንጋኒም፣ ዐይንሐዳ እንዲሁም ቤትጳጼጽ።

22 ድንበራቸውም ታቦርና፣ ሻሕጹማን፣ ቤትሳሚስን ይነካና በዮርዳኖስ ላይ ያቆማል፤ እነዚህ ከነ መንደሮቻቸው ዐሥራ ስድስት ከተሞች ናቸው።

23 እነዚህ ለይሳኮር ነገድ ርስት ሆነው ለየጐሣ ለየጐሣው የተደለደሉ ከተሞችና መንደሮቻቸው ነበሩ።

ለአሴር ነገድ የተመደበው ድርሻ

24 አምስተኛ ዕጣ ለአሴር ነገድ በየጐሣ በየጐሣው ወጣ፤

25 ምድራቸውም የሚከተሉትን ያካትታል፤ሔልቃት፣ ሐሊ፤ ቤጤን፣ አዚፍ፣

26 አላሜሌክ፣ ዓምዓድ እንዲሁም ሚሽአል። ድንበሩ በስተ ምዕራብ ቀርሜሎስንና ሺሖርሊብናትን ይነካል፣

27 ከዚያም በምሥራቅ በኩል ወደ ቤትዳጎን ይመለስና ዛብሎንንና የይፍታሕኤልን ሸለቆ ይዞ ካቡልን በስተ ግራ በመተው በሰሜን በኩል ወደ ቤትዔሜቅና ወደ ንዒኤል ይቃናል።

28 በመቀጠልም ወደ ዔብሮን፣ ወደ ረአብ፣ እንዲሁም ወደ ሐሞንና ወደ ቃና ሽቅብ ወጥቶ እስከ ታላቁ ሲዶና ይደርሳል።

29 ድንበሩ ወደ ራማ ከዞረ በኋላ ወደ ተመሸገው ወደ ጢሮስ ከተማ ታጥፎ ወደ ሖሳ ይመለስና በአክዚብ በኩል ሜድትራኒያን ባሕር ደርሶ ይቆማል፤

30 ይህም የዑማን፣ የአፌቅንና የረአብን ምድር ይጨምራል። በዚህም ሃያ ሁለት ከተሞችና መንደሮቻቸው ይገኛሉ።

31 እነዚህ ለአሴር ነገድ ሆነው በየጐሣው የተደለደሉ ከተሞችና መንደሮቻቸው ነበሩ።

ለንፍታሌም ነገድ የተመደበው ድርሻ

32 ስድስተኛው ዕጣ ለንፍታሌም ነገድ በየጐሣ በየጐሣው ወጣ፤

33 ድንበራቸውም ከሔሌፍና በጸዕነኒም ካለው ከትልቁ የወርካ ዛፍ ይነሣና በአዳ ሚኔቄብና በየብኒኤል አልፎ ወደ ለቁም በመምጣት ዮርዳኖስ ላይ ይቆማል፤

34 ድንበሩ በአዝኖት ታቦር ያልፍና ወደ ምዕራብ በመታጠፍ ሑቆቅ ላይ ይቆማል፤ ይኸው ድንበር በደቡብ ዛብሎንን፣ በምዕራብ አሴርን፣ በምሥራቅ ዮርዳኖስን ይነካል።

35 የተመሸጉትም ከተሞች እነዚህ ናቸው፤ ጺዲም፣ ጼር፣ ሐማት፣ ረቃት፣ ኬኔሬት፣

36 አዳማ፣ ራማ፣ አሶር፣

37 ቃዴስ፣ ኤድራይ፣ ዐይንሐጾር፣

38 ይርኦን፣ ሚግዳልኤል፣ ሖሬም፣ ቤትዓናትና ቤትሳሚስ። እነዚህ ከነ መንደሮቻቸው ዐሥራ ዘጠኝ ከተሞች ናቸው።

39 እነዚህ ለንፍታሌም ነገድ ርስት ሆነው በየጐሣው የተደለደሉ ከተሞችና መንደሮች ነበሩ።

ለዳን ነገድ የተመደበው ድርሻ

40 ሰባተኛው ዕጣ ለዳን ነገድ በየጐሣው ወጣ፤

41 የወረሱትም ምድር የሚከተሉትን ያካትታል፤ጾርዓ፣ ኤሽታኦል፣ ዒርሼሜሽ፣

42 ሸዕለቢን፣ ኤሎን፣ ይትላ፣

43 ኤሎን፣ ተምና፣ አቃሮን፣

44 ኢልተቄ፣ ገባቶን፣ ባዕላት፣

45 ይሁድ፣ ብኔብረቅ፣ ጋትሪሞን፣

46 ሜያርቆንና በኢዮጴ ፊት ለፊት ያለው ርቆን።

47 ነገር ግን የዳን ዘሮች ርስታቸው አልበቃቸውም፣ ወደ ሌሼም ወጥተው አደጋ በመጣል ያዟት፤ ሰዎቹንም በሰይፍ ስለት ፈጅተው ይዞታቸው አደረጓት፤ በዚያው ሰፈሩ፤ ስሟንም ለውጠው በአባታቸው ስም ዳን አሏት።

48 እነዚህ ለዳን ነገድ ርስት ሆነው በየጐሣው የተደለደሉ ከተሞችና መንደሮች ነበሩ።

ለኢያሱ የተመደበው ድርሻ

49 እስራኤላውያን ድርሻ ድርሻቸውን ከያዙ በኋላ፣ ለነዌ ልጅ ለኢያሱ በመካከላቸው ርስት ሰጡት፤

50 እግዚአብሔር ባዘዘውም መሠረት በኰረብታማው የኤፍሬም ምድር የምትገኘውን ተምናሴራ የምትባለውን የፈለጋትን ከተማ ሰጡት፤ እርሱም ከተማዪቱን ሠራ፤ መኖሪያውም አደረጋት።

51 እንግዲህ ካህኑ አልዓዛር፣ የነዌ ልጅ ኢያሱና የእስራኤል ነገድ የየጐሣ መሪዎች ሴሎ ላይ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ፣ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣ ያደላደሉት ርስት ይህ ነው፤ የምድሪቱንም አከፋፈል በዚህ ሁኔታ ፈጸሙ።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24