ኢያሱ 21 NASV

ለሌዋውያን የተመደቡ ከተሞች

1 የሌዋውያን ቤተ ሰብ አለቆች ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር፣ ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱና ወደ ሌሎቹ የእስራኤል ነገድ አባቶች ዘንድ ቀረቡ፤

2 በከነዓን ምድር በሴሎም፣ “እግዚአብሔር የምንኖርባቸውን ከተሞች፣ ከብቶቻችን ከሚሰማሩባቸው ቦታዎች እንድትሰጡን በሙሴ በኩል አዞልን ነበር” አላቸው።

3 ስለዚህ እስራኤላውያን ከወረሱት ምድር ላይ የሚከተሉትን ከተሞችና መሰማሪያዎች እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ለሌዋውያኑ ሰጡ፤

4 የመጀመሪያው ዕጣ ለቀዓት ዘሮች በየጐሣቸው ወጣ፤ የካህኑ የአሮን ዝርያዎች ለሆኑት ሌዋውያን ከይሁዳ፣ ከስምዖንና ከብንያም ነገዶች ዐሥራ ሦስት ከተሞች በዕጣ ተመደቡላቸው።

5 ለቀሩት ለቀዓት ዘሮች ደግሞ ከኤፍሬምና ከዳን ነገድ ጐሣዎች፣ እንዲሁም ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ጐሣዎች ዐሥር ከተሞች በዕጣ ተመደቡላቸው።

6 ለጌርሶን ዝርያዎች ከይሳኮር፣ ከአሴር፣ ከንፍታሌም ነገድ ጐሣዎችና ባሳን ውስጥ ካለው ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ጐሣዎች ዐሥራ ሦስት ከተሞች ተመደቡላቸው።

7 ለሜራሪ ዝርያዎች በየጐሣቸው ከሮቤል፣ ከጋድና ከዛብሎን ነገዶች ዐሥር ከተሞች ተመደቡላቸው።

8 ስለዚህ እስራኤላውያን እግዚአብሔር በሙሴ በኩል ባዘዘው መሠረት፣ እነዚህን ከተሞችና መሰማሪያቸውን ለሌዋውያኑ በዕጣ መደቡላቸው።

9 ከይሁዳና ከስምዖን ነገዶች ደግሞ ከዚህ በታች በስም የተጠቀሱትን ከተሞች በዕጣ መደቡላቸው።

10 እነዚህም ከተሞች የሌዊ ልጆች፣ የቀዓት ጐሣዎች ለሆኑት ለአሮን ዝርያዎች ተመደቡ፤ ይህም የሆነው የመጀመሪያው ዕጣ ለእነርሱ ስለ ወጣላቸው ነበር፤

11 እነርሱም በተራራማው የይሁዳ ምድር ያለችውን ኬብሮን የተባለችውን ቂርያት አርባቅን በዙሪያዋ ካለው መሰማሪያ ጋር ሰጧቸው፤ አርባቅ የዔናቅ አባት ነበረ።

12 ይሁን እንጂ በከተማዪቱ ዙሪያ ያሉትን ዕርሻዎችና መንደሮች ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ ርስት አድርገው ሰጡት።

13 እንደዚሁም ለነፍስ ገዳይ መማጠኛ የሆነችውን ኬብሮንንና ልብናን ከነ ማሰማሪያቸው ለካህኑ ለአሮን ልጆች ሰጧቸው፤

14 ደግሞም የቲርን፣ ኤሽትሞዓን፣

15 ሖሎንን፣ ዳቤርን፣

16 ዐይንን፣ ዮጣንና ቤትሳሚስን ከነ ማሰማሪያቸው ሰጧቸው፤ እነዚህ ዘጠኙ ከተሞች ከሁሉ ነገዶች ይዞታ ላይ ተከፍለው የተሰጡ ናቸው።

17 ከብንያም ነገድ ገባዖን፣ ጌባዕ፣

18 ዓናቶትና አልሞን የተባሉትን አራት ከተሞች ከነ ማሰማሪያዎቻቸው ሰጧቸው።

19 ለካህናቱ ለአሮን ዝርያዎች ከነ ማሰማሪያቸው የተሰጧቸው ከተሞች ዐሥራ ሦስት ነበሩ።

20 የሌዊ ልጅ የቀዓት ጐሣዎች ለሆኑት ለሌሎቹ ደግሞ ከኤፍሬም ነገድ ላይ ተከፍለው የሚከተሉት ከተሞች በዕጣ ተመደቡላቸው።

21 በተራራማው በኤፍሬም ምድርም ለነፍሰ ገዳይ መማጠኛ የሆነችው ሴኬምና ጌዝር፣

22 ቂብጻይሞና ቤትሖሮን ከነመሠማሪያዎቻቸው አራት ከተሞች ተሰጡአቸው።

23 እንዲሁም ከዳን ነገድ ኤልተቄን፣ ገባቶን፤

24 ኤሎንና ጋትሪሞን ከነመሰማሪያዎቻቸው አራት ከተሞች ተሰጧቸው።

25 ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ደግሞ ታዕናክና ጋትሪሞን ከነ ማሰማሪያዎቻቸው ሁለት ከተሞች ተሰጧቸው።

26 እነዚህ ዐሥር ከተሞች ሁሉ ከነ ማሰማሪያዎቻቸው ለተቀሩት የቀዓት ጐሣዎች ተሰጧቸው።

27 የጌርሶን ወገኖች ለሆኑት ለሌሎቹ የሌዊ ጐሳዎች የተሰጧቸው የሚከተሉት ናቸው፤ከምናሴ ነገድ እኩሌታ በባሳን ውስጥ ለነፍሰ ገዳይ መማጠኛ የሆነችው ከተማ ጎላንና በኤሽትራ እነዚህ ሁለት ከተሞች ከነመሰማሪያዎቻቸው፤

28 ከይሳኮር ነገድ፣ቂሶን፣ ዳብራት፣

29 የርሙትና ዓይን ጋኒም፣ እነዚህ አራት ከተሞች ከነመሰማሪያዎቻቸው፤

30 ከአሴር ነገድ፣ሚሽአል፣ ዓብዶን፣

31 ሔልቃትና ረአብ እነዚህ አራት ከተሞች ከነመሰማሪያዎቻቸው፤

32 ከንፍታሌም ነገድ፣በገሊላ ውስጥ ለነፍሰ ገዳይ መማጠኛ የሆነችው ከተማ ቃዴስ፣ ሐሞትዶርና ቀርታን እነዚህ ሦስት ከተሞች ከነመሰማሪያዎቻቸው፤

33 ለጌድሶናውያን ጐሣዎች የተመደቡት ከተሞች ሁሉ ከነ ማሰማሪያዎቻቸው ዐሥራ ሦስት ነበሩ።

34 የሜራሪ ጐሣዎች ለሆኑት ለተቀሩት ሌዋውያን የተሰጧቸው የሚከተሉት ናቸው፤ከዛብሎን ነገድ ዮቅንዓም፣ ቀርታ፣

35 ዲሞናና ነህላል፣ እነዚህ አራት ከተሞች ከነመሰማሪያዎቻቸው፤

36 ከሮቤል ነገድ፣ቦሶር፣ ያሀጽ፣

37 ቅዴሞትና ሜፍዓት፣ እነዚህ አራት ከተሞች ከነመሰማሪያዎቻቸው፤

38 ከጋድ ነገድ፣በገለዓድ ውስጥ ለነፍሰ ገዳይ መማጠኛ የሆነችው ከተማ ራሞት መሃናይም፣

39 ሐሴቦንና ኢያዜር፣ እነዚህ አራት ከተሞች ከነመሰማሪያዎቻቸው፦

40 የሜራሪ ጐሣዎች ለሆኑት ለተቀሩት ሌዋውያን የተመደቡት ከተሞች ሁሉ ዐሥራ ሁለት ነበሩ።

41 እንግዲህ እስራኤላውያን ርስት አድርገው ከያዙት ምድር ለሌዋውያኑ የተሰጧቸው ከተሞች ከነ ማሰማሪያዎቻቸው ባጠቃላይ አርባ ስምንት ነበሩ።

42 እነዚህም ከተሞች እያንዳንዳቸው በዙሪያቸው ማሰማሪያዎች ነበሯቸው፤ ማሰማሪያ የሌለው ከተማ አልነበረም።

43 ስለዚህ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻቸው ይሰጣቸው ዘንድ የማለላቸውን ምድር ሁሉ ለእስራኤል ሰጠ፤ እነርሱም ምድሪቱን ወረሱ፣ መኖሪያቸውም አደረጓት።

44 እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻቸው እንደ ማለላቸው በዙሪያቸው ካሉት አሳረፋቸው፤ አንድም ጠላት ሊቋቋማቸው አልቻለም፤ እግዚአብሔር ጠላቶቻቸውን ሁሉ አሳልፎ በእጃቸው ሰጥቶአቸዋልና።

45 እግዚአብሔር ለእስራኤል ቤት ከሰጠው መልካም የተስፋ ቃል አንዳችም አልቀረም፤ ሁሉም ተፈጽሞአል።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24