1 ከዚያም እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤
2 “በሙሴ በኩል በነገርኋችሁ መሠረት የመማጠኛ ከተሞች እንዲለዩ ለእስራኤላውያን ንገራቸው፤
3 ሳያስበው ድንገት ሰው የገደለ ማንኛውም ሰው ወደዚያ በመሸሽ ከደም ተበቃዩ እንዲያመልጥ ከተማዪቱ መጠለያ ትሁን።
4 “ገዳዩ ከነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ በሚሸሽበት ጊዜ፣ በከተማዪቱ መግቢያ በር ላይ ቆሞ ጒዳዩን ለከተማዪቱ ሽማግሌዎች ይንገራቸው፤ ከዚያም እነርሱ ወደ ከተማቸው አስገብተው የሚኖርበትን ስፍራ ሰጥተውት አብሮአቸው ይቀመጥ።
5 ደም ተበቃዩ ተከታትሎት ቢመጣ፣ ሆን ብሎና በክፋት ተነሣሥቶ ወንድሙን የገደለው ባለመሆኑ፣ ሰዎቹ ነፍሰ ገዳዩን አሳልፈው አይስጡት።
6 በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቀርብና በዚያ ጊዜ የሚያገለግለው ሊቀ ካህናት እስኪሞት ድረስ በዚያች ከተማ ይቆይ። ከዚያም ወደ ቤቱ፣ ሸሽቶ ወደ መጣበት ከተማ ሊመለስ ይችላል።”
7 ስለዚህም በኰረብታማው በንፍታሌም ምድር በገሊላ ቃዴስን፣ በኰረብታማው በኤፍሬም ምድር ሴኬምን፣ በኰረብታማው በይሁዳ ምድር ኬብሮን የምትባለውን ቂርያት አርባቅን ለዩ።
8 እንደዚሁም ከዮርዳኖስ ማዶ ከኢያሪኮ በስተምስራቅ በሮቤል ነገድ ይዞታ ውስጥ ከፍታ ባለው ምድረ በዳ ያለችውን ቦሶርን፣ በጋድ ነገድ ይዞታ ውስጥ ባለችው በገለዓድ የምትገኘውን ራሞትንና በምናሴ ነገድ ይዞታ ውስጥ በባሳን የምትገኘውን ጎላንን ለዩ።
9 ሳያስበው በድንገት ሰው የገደለ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በመካከላቸው የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ ወደ ተለዩት ከተሞች መሸሽ ይችላል፤ በማኅበሩ ፊት ከመቆሙ አስቀድሞም በደም ተበቃዩ መገደል የለበትም።