ኢያሱ 14 NASV

ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ስላለው ምድር አከፋፈል

1 ካህኑ አልዓዛር፣ የነዌ ልጅ ኢያሱና የእስራኤል የየነገዱ ጐሣ አባቶች የደለደሉላቸው፣ እስራኤላውያንም በከነዓን ምድር የወረሱት ርስት ይህ ነው።

2 ርስታቸውም እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት፣ ለዘጠኙ ነገድና ለእኩሌታው ነገድ በዕጣ ተከፋፈለ።

3 ሙሴ ለሁለቱ ነገድና ለእኩሌታው፣ የዮርዳኖስን ምሥራቅ ክፍል ርስት አድርጎ ሰጣቸው፤ ሌዋውያኑ ግን አብረዋቸው እንዲካፈሉ አላደረገም፤

4 የዮሴፍ ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ሁለት ነገዶች ሆነው ነበርና፤ ለሌዋውያኑ ግን ከሚኖሩባቸው ከተሞች እንዲሁም ለበግ፣ ለፍየልና ለከብት መንጎቻቸው መሰማሪያ እንዲሆን አብሮ የተከለለላቸውን ምድር ብቻ እንጂ ሌላ አልሰጣቸውም፤

5 ስለዚህ እስራኤላውያን እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት፣ ምድሪቱን ተካፈሉ።

ኬብሮን ለካሌብ ተሰጠች

6 የይሁዳም ሰዎች በጌልገላ ወደ ኢያሱ ቀረቡ፤ ከዚያም የቄኔዛዊው የዮፎኒ ልጅ ካሌብ እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር በቃዴስ በርኔ ስለ አንተና ስለ እኔ፣ የአምላክ ሰው ለሆነው ለሙሴ የተናገረውን ታውቃለህ።

7 የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ምድሪቱን እንድሰልል ከቃዴስ በርኔ በላከኝ ጊዜ የአርባ ዓመት ሰው ነበርሁ፤ እኔም ትክክለኛውን ማስረጃ ይዤለት መጣሁ፤

8 አብረውኝ ወደዚያ የወጡት ወንድሞቼ ግን፣ የሕዝቡ ልብ በፍርሃት እንዲቀልጥ አደረጉ፤ ሆኖም እኔ አምላኬን እግዚአብሔርን በፍጹም ልቤ ተከተልሁት።

9 ስለዚህም ሙሴ በዚያች ዕለት፣ ‘አምላኬን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ ተከትለኸዋልና እግርህ የረገጣት ምድር ለዘላለም የአንተና የዘርህ ርስት ትሆናለች’ ብሎ ማለልኝ።

10 “አሁንም እነሆ፤ ልክ እግዚአብሔር እንዳለው ይህን ለሙሴ ከተናገረበት ጊዜ አንሥቶ እስራኤል በምድረ በዳ ሲንከራተት እኔን አርባ አምስት ዓመት በሕይወት ጠብቆ አኑሮኛል፤ ይኸው ዛሬ ሰማንያ አምስት ዓመት ሆነኝ።

11 ሙሴ በላከኝ ጊዜ የነበረኝ ብርታት ዛሬም አብሮኝ አለ፤ ልክ እንደዚያን ጊዜ ሁሉ አሁንም ወደ ጦርነት ለመሄድ ኀይሉም ብርታቱም አለኝ።

12 አሁንም እግዚአብሔር በዚያች ዕለት ቃል የገባልኝን ይህችን ኰረብታማ አገር ሰጠኝ። ዔናቃውያን በዚያ እንደ ነበሩና ከተሞቻቸውም ታላላቅና የተመሸጉ እንደሆኑ ያን ጊዜ አንተው ራስህ ሰምተሃል፤ ሆኖም ልክ እርሱ እንዳለው በእግዚአብሔር እርዳታ አሳድጄ አወጣቸዋለሁ።”

13 ከዚያም ኢያሱ የዮፎኒን ልጅ ካሌብን ባረከው፤ ኬብሮንንም ርስት አድርጎ ሰጠው።

14 ስለዚህም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኬብሮን የቄኔዛዊው የዮፎኒ ልጅ የካሌብ ርስት ሆነች፤ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ ተከትሎአልና።

15 ኬብሮን ቀድሞ ከዔናቃውያን ሁሉ ታላቅ በሆነው በአርባቅ ስም ቂርያት አርባቅ ተብላ ትጠራ ነበር።ከዚያም ምድሪቱ ከጦርነት ዐረፈች።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24