ኢያሱ 15 NASV

ለይሁዳ ነገድ የተመደበው ድርሻ

1 ለይሁዳ ነገድ በየጐሣቸው በዕጣ የተመደበው ድርሻ እስከ ኤዶም ምድር የሚወርድ ሲሆን፣ በስተ ደቡብ መጨረሻ እስከ ጺን ምድረ በዳ ድረስ ይዘልቃል።

2 የደቡብ ወሰናቸው፣ ከጨው ባሕር ደቡባዊ ጫፍ ካለው የባሕር ወሽመጥ ይነሣል፤

3 ከዚያም የአቅረቢምን መተላለፊያ በማቋረጥ በጺን በኩል እስከ ቃዴስ በርኔ ደቡባዊ ክፍል ይደርሳል፤ ደግሞም ሐጽሮንን አልፎ ወደ አዳር ይወጣና ወደ ቀርቃ ይታጠፋል፤

4 በአድሞን በኩል አድርጎም ወደ ግብፅ ደረቅ ወንዝ ይገባና መቆሚያው ባሕሩ ይሆናል፤ እንግዲህ በደቡብ በኩል ያለው ወሰናቸው ይህ ነው።

5 በምሥራቅ በኩል ያለው ወሰናቸው ደግሞ የጨው ባሕር ሲሆን፣ ይህም የዮርዳኖስ ወንዝ እስከሚሠርግበት ይደርሳል።በሰሜን በኩል ያለው ወሰንም የዮርዳኖስ ወንዝ ከሚሠርግበት የባሕር ወሽመጥ ይነሣና

6 ሽቅብ ወደ ቤትሖግላ ይወጣል፤ ከዚያም በሰሜናዊው ቤትዓረባ በኩል አድርጎ የሮቤል ልጅ የቦሀን ድንጋይ እስካለበት ይደርሳል።

7 ከዚያም ድንበሩ ከአኮር ሸለቆ ወደ ዳቤር ይወጣና ከወንዙ በስተ ደቡብ ባለው በአዱሚም መተላለፊያ ፊት ለፊት አድርጎ በስተ ሰሜን ወደ ጌልገላ ይታጠፋል፤ በዓይንሳሚስ ምንጭ በኩል አልፎም ወደ ዓይንሮጌል ይወጣል።

8 እንደዚሁም የሄኖምን ልጅ ሸለቆ አልፎ ይሄድና የኢያቡሳውያን ከተማ እስከ ሆነችው እስከ ኢየሩሳሌም ደቡባዊ ተረተር በመዝለቅ፣ በራፋይም ሸለቆ ሰሜን ጫፍ በኩል አድርጎ ከሄኖም ሸለቆ በስተ ምዕራብ ካለው ኰረብታ አናት ላይ ይደርሳል።

9 ከዚያም በመቀጠል ከተራራው አናት ተነሥቶ ወደ ኔፍቶ ምንጮች በማምራት፣ በዔፍሮን ተራራ ላይ ያሉትን ከተሞች አልፎ ይወጣና ቂርያትይዓሪም ተብሎ ወደሚጠራው ወደ በኣላ ቊልቊል ይወርዳል፤

10 ከዚያም ከበኣላ በምዕራብ በኩል አድርጎ ወደ ሴይር ይታጠፍና ክሳሎን ተብሎ በሚጠራው በይዓሪም ኰረብታ ሰሜናዊ ተረተር አልፎ ቊልቊል ወደ ቤትሳሚስ በመውረድ ወደ ተምና ይሻገራል።

11 ደግሞም በአቃሮን ሰሜናዊ ተረተር አድርጎ ወደ ሽክሮን ይታጠፍና በበኣላ ተራራ ላይ አልፎ እስከ የብኒኤል ይደርሳል፤ ከዚህ በኋላ ወሰኑ ባሕሩ ላይ ይቆማል።

12 የምድሪቱ ምዕራባዊ ወሰን የታላቁ ባሕር ጠረፍ ነው።እንግዲህ በየጐሣው የተደለደለውን የይሁዳን ሕዝብ በዙሪያው የከበቡት ወሰኖቹ እነዚሁ ናቸው።

13 ኢያሱ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት፣ ከይሁዳ ድርሻ ላይ ከፍሎ ኬብሮን የተባለችውን ቂርያት አርባቅን ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ ሰጠው፤ አርባቅም የዔናቅ አባት ነበረ።

14 ካሌብም ሦስቱን የዔናቅን ዘሮች ሴሲንን፣ አኪመንንና ተላሚንን ከኬብሮን አሳደዳቸው፤

15 ከዚያም በዳቤር ሕዝብ ላይ ዘመተ፤ ዳቤር ቀድሞ ቂርያትሤፍር ትባል ነበር።

16 ካሌብ፣ “ቂርያትሤፍርን ወግቶ ለሚይዝ ሰው ልጄን ዓክሳን እድርለታለሁ” አለ።

17 ስለዚህ የካሌብ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ከተማዪቱን ያዛት፤ ካሌብም ልጁን ዓክሳን ዳረለት።

18 ዓክሳ ወደ ጎቶንያል በመጣች ጊዜም፣ ከአባትዋ ላይ የእርሻ መሬት እንዲለምን አጥብቃ ነገረችው። ከአህያዋ ላይ እንደ ወረደች ካሌብ፣ “ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ?” ሲል ጠየቃት።

19 እርስዋም፣ “እባክህ፤ በጎ ነገር አድርግልኝ፤ በኔጌብ መሬት እንደ ሰጠኸኝ ሁሉ፣ አሁንም የውሃ ምንጭ ጉድጓዶች ስጠኝ” አለችው፤ ካሌብም የላይኛውንና የታችኛውን ምንጮች ሰጣት።

20 ለይሁዳ ነገድ በየጐሣቸው የተሰጣቸው ርስት ይህ ነው፤

21 በኔጌብ አካባቢ በኤዶም ድንበር ላይ በወሰኑ ጫፍ የሚገኙት የይሁዳ ነገድ ደቡባዊ ከተሞች እነዚህ ነበሩ፤ቀብስኤል፣ ዔዴር፣ ያጉር፣

22 ቂና፣ ዲሞና፣ ዓድዓዳ፣

23 ቃዴስ፣ ሐጾር፤ ዩትናን፣

24 ዚፍ፣ ጤሌም፣ በዓሎት፣

25 ሐጾርሐዳታ፣ ሐጾር የምትባለው ቂርያትሐጾር

26 አማም፣ ሽማዕ፣ ሞላዳ፣

27 ሐጻርጋዳ፣ ሐሽሞን፣ ቤትጳሌጥ፣

28 ሐጸር ሹዓል፣ ቤርሳቤህ፣ ቢዝዮትያ

29 በኣላ፣ ዒዪም፣ ዓጼም፣

30 ኤልቶላድ፣ ኪሲል፣ ሔርማ፣

31 ጺቅላግ፣ ማድማና፣ ሳንሳና

32 ልባዎት፣ ሺልሂም፣ ዓይንና ሪሞን ናቸው፤ ባጠቃላይም ከተሞቹና መንደሮቻቸው ሃያ ዘጠኝ ናቸው።

33 በምዕራቡ በኰረብታዎች ግርጌ ያሉት ደግሞ እነዚህ ናቸው፤ ኤሽታኦል፤ ጾርዓ፣ አሽና

34 ዛኖዋ፣ ዓይንገኒም፣ ታጱዋ፣ ዓይናም፣

35 የርሙት፣ ዓዶላም፣ ሰኰት፣ ዓዜቃ፣

36 ሽዓራይም፣ ዓዲታይም፣ ግዴራ፣ ግዴሮታይም ናቸው፤ ከተሞቹም ከነ መንደሮቻቸው ዐሥራ አራት ናቸው።

37 ጽናን፣ ሐዳሻ፣ ሚግዳልጋድ፣

38 ዲልዓን፣ ምጽጳ፣ ዮቅትኤል፣

39 ለኪሶ፣ ቦጽቃት፣ ዔግሎን፣

40 ከቦን፣ ለሕማስ፣ ኪትሊሽ፣

41 ግዴሮት፣ ቤትዳጎን፣ ናዕማና መቄዳ ናቸው፤ ከተሞቹም ከነ መንደሮቻቸው ዐሥራ ስድስት ናቸው።

42 ልብና፣ ዔትር፣ ዓሻን

43 ይፍታሕ፣ አሽና፣ ንጺብ፣

44 ቅዒላ፣ አክዚብና መሪሳ ናቸው፤ ከተሞቹም ከነ መንደሮቻቸው ዘጠኝ ናቸው።

45 አቃሮን በዙሪያዋ ካሉ ሰፈሮችና መንደሮቿ ጋር፣

46 እንዲሁም ከአቃሮን በስተ ምዕራብ በአሽዶድ አካባቢ ያሉ ሰፈሮችና መንደሮቻቸው ሁሉ፣

47 አሽዶድ በዙሪያዋ ካሉ ሰፈሮችና መንደሮች ጋር፣ ጋዛ እስከ ግብፅ ደረቅ ወንዝና እስከ ታላቁ ባሕር ጠረፍ በመለስ ካሉት ሰፈሮቿና መንደሮቿ ጋር።

48 በኰረብታማዋም አገር የሚገኙ ከተሞች ደግሞ እነዚህ ናቸው፤ ሳምር፣ የቲር፣ ሶኮ

49 ደና፣ ዳቤር የምትባለው ቂርያትስና

50 ዓናብ፣ ኤሽትሞዓ፣ ዓኒም፣

51 ጎሶም፣ ሖሎንና ጊሎ፤ እነዚህም ዐሥራ አንዱ ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው።

52 አራብ፣ ዱማ፣ ኤሽዓን፣

53 ያኒም፣ ቤትታጱዋ፣ አፌቃ

54 ሑምጣ፣ ኬብሮን የተባለችው ቂርያትአርባቅና ጺዖር ናቸው፤ እነዚህም ዘጠኝ ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው።

55 ማዖን፣ ቀርሜሎስ፣ ዚፍ፣ ዩጣ

56 ኢይዝራኤል፣ ዮቅድዓም፣ ዛኖዋሕ፣

57 ቃይን፣ ጊብዓና ተምና ናቸው፤ እነዚህም ዐሥር ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው።

58 ሐልሑል፣ ቤትጹር፣ ጌዶር፣

59 ማዕራት፣ ቤትዓኖትና ኤልትቆን ናቸው፤ እነዚህም ስድስት ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው።

60 ቂርያትይዓሪም የተባለችው ቂርያ ትበኣልና ረባት፤ እነዚህም ሁለት ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው።

61 በምድረ በዳው ደግሞ እነዚህ ናቸው፤ ቤትዓረባ፣ ሚዲን፣ ስካካ፣

62 ኒብሻን፣ የጨው ከተማና ዓይንጋዲ፤ እነዚህም ስድስት ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው።

63 ነገር ግን የይሁዳ ዘሮች በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያን ከቦታቸው ሊያስለቅቋቸው አልቻሉም፤ ኢያቡሳውያንም እስከ ዛሬ ድረስ ከይሁዳ ሕዝብ ጋር በኢየሩሳሌም አብረው ይኖራሉ።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24