ኢያሱ 22:3-9 NASV

3 ከረጅም ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ወንድሞቻችሁን አልተዋችሁም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ተልእኮ በሚገባ ተወጥታችኋል።

4 አሁንም አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ወንድሞቻችሁን አሳርፎአቸዋል፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ከዮርዳኖስ ማዶ ርስት አድርጎ በሰጣችሁ ምድር ወዳለው ቤታችሁ ተመለሱ።

5 የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ፣ አምላካችሁን እግዚአብሔርን እንድትወዱ፣ በመንገዱ ሁሉ እንድትሄዱ፣ ትእዛዙን እንድትፈጽሙ፣ እርሱንም አጥብቃችሁ እንድትይዙት እንዲሁም በፍጹም ልባችሁ፣ በፍጹም ነፍሳችሁ እንድታገለግሉት የሰጣችሁን ትእዛዙንና ሕጉን ነቅታችሁ ጠብቁ።”

6 ከዚያም ኢያሱ መርቆ አሰናበታቸው፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ተመለሱ።

7 ሙሴ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ በባሳን ምድር ርስት ሰጥቶአቸው ነበር፤ ለቀረው እኩሌታ ደግሞ ኢያሱ ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ከወንድሞቻቸው ጋር ርስት ሰጣቸው። ኢያሱ ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ባሰናበታቸው ጊዜ መረቃቸው፤

8 እንዲህም አላቸው፤ “ብዙ ሀብት ይዛችሁ ማለትም አያሌ የከብት መንጋ፣ ብርና ወርቅ፣ ናስና ብረት እንዲሁም ቊጥሩ እጅግ የበዛ ልብስ ይዛችሁ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ፤ ከጠላት የተገኘውንም ይህን ምርኮ ከወንድሞቻችሁ ጋር ተካፈሉት” አላቸው።

9 ስለዚህ የሮቤልና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ እስራኤላውያንን ከነዓን ውስጥ ባለችው በሴሎ ትተው፣ በእግዚአብሔር ትእዛዝ በሙሴ አማካይነት ወደ ተቀበሏት ርስታቸው፣ ወደ ገለዓድ ምድር ተመለሱ።