ኢያሱ 22:9-15 NASV

9 ስለዚህ የሮቤልና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ እስራኤላውያንን ከነዓን ውስጥ ባለችው በሴሎ ትተው፣ በእግዚአብሔር ትእዛዝ በሙሴ አማካይነት ወደ ተቀበሏት ርስታቸው፣ ወደ ገለዓድ ምድር ተመለሱ።

10 የሮቤልና የጋድ እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ በከነዓን ምድር ወዳለችው፣ ዮርዳኖስ አጠገብ ወደምትገኘው ገሊሎት ወደተባለች ስፍራ ሲደርሱ በወንዙ አጠገብ ግዙፍ መሠዊያ ሠሩ።

11 የእስራኤላውያን ይዞታ በሆነችው በከነዓናውያን ምድር ወሰን በገሊሎት ላይ መሠዊያ መሥራታቸውን፣ ሌሎቹ እስራኤላውያን በሰሙ ጊዜ፣

12 በእነርሱ ላይ ለመዝመት፣ የእስራኤል ማኅበር ሁሉ በሴሎ ተሰበሰቡ።

13 ስለዚህም እስራኤላውያን የካህኑ የአልዓዛርን ልጅ ፊንሐስን በገለዓድ ምድር ወደሚኖሩት ወደ ሮቤልና ወደ ጋድ እንዲሁም ወደ ምናሴ ነገድ እኩሌታ ላኩ፤

14 ከእርሱም ጋር እያንዳንዱን የእስራኤልን ነገድ የሚወክሉ ዐሥር አለቆች አብረው ላኩ፤ እነዚህም እያንዳንዳቸው ከእስራኤላውያን ጐሣዎች የተውጣጡ የየቤተ ሰቡ አለቆች ነበሩ።

15 እነርሱም በገለዓድ ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤላውያን፣ ወደ ጋዳውያንና ወደ ምናሴ ነገድ እኩሌታ ሄደው እንዲህ አሏቸው፤