ኢያሱ 8:1-6 NASV

1 ከዚያም እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “አትፍራ፤ አትደንግጥ፤ ሰራዊቱን ሁሉ ይዘህ በመውጣት ጋይን ውጋ፤ የጋይን ንጉሥ፣ ሕዝቡን፣ ከተማውንና ምድሩን አሳልፌ በእጅህ ሰጥቼሃለሁና።

2 በኢያሪኮና በንጉሥዋ ላይ ያደረግኸውንም ሁሉ፣ በጋይና በንጉሥዋ ላይ ትደግመዋለህ፤ በዚህ ጊዜ ግን ምርኮውንና ከብቱን ለራሳችሁ ታደርጉታላችሁ፤ ታዲያ ከከተማዪቱ በስተ ጀርባ የደፈጣ ጦር አዘጋጅ።”

3 ስለዚህ ኢያሱና ሰራዊቱ በሙሉ ጋይን ለመውጋት ወጡ፤ ኢያሱም ምርጥ ከሆኑት ተዋጊዎቹ ሠላሳ ሺህ ጦር አዘጋጅቶ በሌሊት ላካቸው፤

4 እንዲህ የሚል ትእዛዝም ሰጣቸው፤ “እነሆ፤ ከከተማዪቱ በስተ ጀርባ ታደፍጣላችሁ፤ ከከተማዪቱ አትራቁ፤ ሁላችሁም ነቅታችሁ ተጠባበቁ፤

5 እኔና አብረውኝ ያሉት ሁሉ ወደ ከተማዪቱ እንጠጋለን፤ ሰዎቹ ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሊወጉን ወደኛ ሲመጡ፤ እኛ ደግሞ እንሸሻለን፤

6 እነርሱም፣ ‘ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት አሁንም ከእኛ በመሸሽ ላይ ናቸው’ በማለት ከከተማዪቱ እስክና ርቃቸው ድረስ ይከታተሉናል፤ በዚህ ሁኔታ እኛም እንሸሻለን፣