ዘዳግም 16:1-7 NASV

1 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በአቢብ ወር ከግብፅ በሌሊት ስላወጣህ፣ የአቢብን ወር ጠብቅ፤ የአምላክህን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ፋሲካ አክብርበት።

2 እግዚአብሔር (ያህዌ) ለስሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ በሚመርጠው ስፍራ ከበግና ከፍየል ወይም ከመንጋህ አንዱን እንስሳ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፋሲካ አድርገህ ሠዋው።

3 ከቦካ ቂጣ ጋር አትብላው፤ ከግብፅ የወጣኸው በችኮላ ነውና ከግብፅ የወጣህበትን ጊዜ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ታስብ ዘንድ የመከራ ቂጣ ሰባት ቀን ብላ።

4 በምድርህ ሁሉ ላይ በአንተ ዘንድ ለሰባት ቀን እርሾ አይገኝ፤ በመጀመሪያው ዕለት ምሽት ከምትሠዋውም ላይ ማናቸውንም ሥጋ ጧት ድረስ እንዲቈይ አታድርግ።

5 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ በማናቸውም ከተማ ፋሲካን መሠዋት አይገባህም፤

6 ነገር ግን ለስሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ፣ ፀሓይ ስትጠልቅ ምሽቱ ላይ ከግብፅ በወጣህበት ሰዓት ዓመታዊ መታሰቢያ በዚያ ፋሲካን ሠዋ።

7 ሥጋውንም ጠብሰህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ ብላ፤ ሲነጋም ወደ ድንኳንህ ተመልሰህ ሂድ።