ዘዳግም 23:18-24 NASV

18 ለዝሙት አዳሪ ሴት ወይም ለወንደቃ የተከፈለውን ዋጋ ለማናቸውም ስእለት አድርገህ ለመስጠት ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቤት አታምጣ፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሁለቱንም ይጸየፋቸዋልና።

19 የገንዘብ፣ የእህል ወይም የማንኛውንም ነገር ወለድ ለማግኘት ለወንድምህ በወለድ አታበድር።

20 ባዕድ ለሆነ ሰው ወለድ ማበደር ትችላለህ፤ ነገር ግን ልትወርሳት በምትገባባት ምድር እጅህ በሚነካው በማናቸውም ነገር አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እንዲባርክህ ለእስራኤላዊ ወንድምህ በወለድ አታበድረው።

21 ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ስእለት ከተሳልህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አጥብቆ ከአንተ ይሻዋልና፣ ኀጢአት እንዳይሆንብህ ለመክፈል አትዘግይ።

22 ሳትሳል ብትቀር ግን በደለኛ አትሆንም።

23 በአንደበትህ የተናገርኸውን ሁሉ ለመፈጸም ጠንቃቃ ሁን፤ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በገዛ አንደበትህ ፈቅደህ ስእለት ተስለሃልና።

24 ወደ ባልንጀራህ የወይን ተክል ቦታ በምትገባበት ጊዜ፣ ያሰኘህን ያህል መብላት ትችላለህ፤ ነገር ግን አንዳችም በዕቃህ አትያዝ።