1 በሰዎች መካከል ጠብ ቢነሣና ወደ ፍርድ አደባባይ ቢሄዱ፣ ዳኞች ተበዳይን ነጻ፣ በዳይን ግን ጥፋተኛ በማድረግ የፍርድ ውሳኔ ይስጡ።
2 በደለኛው ሰው መገረፍ የሚገባው ሆኖ ከተገኘ፣ ዳኛው መሬት ላይ ያጋድመው፤ ለጥፋቱ ተመጣጣኝ የሆነ ግርፋት እርሱ ባለበት ይገረፍ።
3 ሆኖም ግርፋቱ ከአርባ የሚበልጥ አይሁን፤ ከዚህ ካለፈ ግን፣ ወንድምህ በፊትህ የተዋረደ ይሆናል።
4 እህል እያበራየያለውን በሬ አፉን አትሰር።
5 ወንድማማቾች በአንድነት ቢኖሩና ከእነርሱ አንዱ ወንድ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፣ የሟቹ ሚስት ከቤተ ሰቡ ውጭ ባል ማግባት የለባትም። የባሏ ወንድም ይውሰዳትና ያግባት፤ የዋርሳነት ግዴታውንም ይፈጽምላት።
6 በመጀመሪያ የምትወልደውም ልጅ ስሙ ከእስራኤል ፈጽሞ እንዳይጠፋ በሟች ወንድሙ ስም ይጠራ።