ዘዳግም 25:3-9 NASV

3 ሆኖም ግርፋቱ ከአርባ የሚበልጥ አይሁን፤ ከዚህ ካለፈ ግን፣ ወንድምህ በፊትህ የተዋረደ ይሆናል።

4 እህል እያበራየያለውን በሬ አፉን አትሰር።

5 ወንድማማቾች በአንድነት ቢኖሩና ከእነርሱ አንዱ ወንድ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፣ የሟቹ ሚስት ከቤተ ሰቡ ውጭ ባል ማግባት የለባትም። የባሏ ወንድም ይውሰዳትና ያግባት፤ የዋርሳነት ግዴታውንም ይፈጽምላት።

6 በመጀመሪያ የምትወልደውም ልጅ ስሙ ከእስራኤል ፈጽሞ እንዳይጠፋ በሟች ወንድሙ ስም ይጠራ።

7 ሆኖም ግን አንድ ሰው የወንድሙን ሚስት ለማግባት ባይፈልግ፣ ሴትዮዋ በከተማዋ በር ወዳሉት ሽማግሌዎች ሄዳ፣ “የባለቤቴ ወንድም የወንድሙን ስም በእስራኤል ለማስጠራት አልፈለገም፤ የዋርሳነት ግዴታውንም አልፈ ጸመልኝም” ትበላቸው።

8 ከዚያም የከተማው ሽማግሌዎች ያን ሰው ጠርተው ያነጋግሩት፤ እርሱም፣ “እርሷን ላገባት አልፈልግም” ብሎ በሐሳቡ ቢጸና፣

9 የወንድሙም ሚስት በሽማግሌዎች ፊት ወደ እርሱ ቀርባ፣ የአንድ እግሩን ጫማ በማውለቅ በፊቱ ላይ ትትፋበትና “የወንድሙን ቤት በማይሠራ ሰው ላይ እንዲህ ያለው ድርጊት ይፈጸምበታል” ትበል።