ዘዳግም 26:11-17 NASV

11 ከዚያም አንተ፣ ሌዋዊውና በመካከልህ የሚኖረው መጻተኛ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለአንተና ለቤትህ በሰጠው በጎ ነገር ሁሉ ደስ ይበላችሁ።

12 የዐሥራት ዓመት የሆነውን የሦስተኛውን ዓመት ምርት አንድ ዐሥረኛ ለይተህ ካወጣህ በኋላ በየከተሞችህ ውስጥ በልተው እንዲጠግቡ፣ ለሌዋዊው፣ ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ስጣቸው፤

13 ከዚያ በኋላ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እንዲህ በል፤ “በሰጠኸኝ ትእዛዝ መሠረት የተቀደሰውን ክፍል ከቤቴ አውጥቼ ለሌዋዊው፣ ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ሰጥቻለሁ። ከትእዛዝህ አልወጣሁም፤ አንዱንም አልረሳሁም።

14 በሐዘን ላይ ሳለሁ፣ ከተቀደሰው ክፍል ላይ ምንም አልበላሁም፤ ባልነጻሁበትም ጊዜ ከዚሁ ላይ ያነሣሁትም ሆነ ለሙታን ያቀረብሁት ምንም ነገር የለም፤ አምላኬን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ታዝዣለሁ፤ ያዘዝኸኝንም ሁሉ ፈጽሜአለሁ።

15 ከቅዱስ ማደሪያህ ከሰማይ ተመልከት፤ ሕዝብህን እስራኤልንና ለአባቶቻችን በመሓላ ቃል በገባኸው መሠረት፣ ለእኛ የሰጠኸንን ይህችን ማርና ወተት የምታፈሰውን ምድር ባርክ።”

16 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ይህን ሥርዐትና ሕግ ትጠብቅ ዘንድ ዛሬ ያዝሃል፤ አንተም በፍጹም ልብህ፣ በፍጹምም ነፍስህ ትፈጽመው ዘንድ ተጠንቀቅ።

17 እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) እንደሆነ በመንገዱም እንደምትሄድ፣ ሥርዐቱን፣ ትእዛዙንና ሕጉን እንደምትጠብቅና እንደምትታዘዝለት በዛሬዪቱ ዕለት ተናግረሃል።