ዘዳግም 29:22-28 NASV

22 የሚቀጥለው ትውልድ ከእናንተ በኋላ የሚተኩት ልጆቻችሁና ከሩቅ አገር የሚመጡ እንግዶች በምድሪቱ የደረሰውን ታላቅ መቅሠፍትና እግዚአብሔር (ያህዌ) ያመጣባቸውን በሽታዎች ያያሉ።

23 ምድሪቱ በሙሉ የተቃጠለ ጨውና ዲን ዐመድ ትሆናለች። አንዳች ነገር አይተከልባትም፤ ምንም ነገር አያቈጠቊጥባትም፤ የሚያድግ ተክል አይገኝባትም። የሚደርስባት ውድመት እግዚአብሔር (ያህዌ) በታላቅ ቊጣ እንደ ገለባበጣቸው እንደ ሰዶምና ገሞራ፣ እንደ አዳማና ሲባዮ ጥፋት ይሆናል።

24 አሕዛብም ሁሉ፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) በዚች ምድር ላይ ይህን ለምን አደረገባት? ይህ አስፈሪና የሚነድ ቊጣስ ለምን መጣባት?” ብለው ይጠይቃሉ።

25 መልሱም፣ “የአባቶቻቸው አምላክ (ኤሎሂም) ከግብፅ ምድር ባወጣቸው ጊዜ፣ ከእነርሱ ጋር የገባውን ኪዳን ሕዝቡ ስለ ተዉ ነው።

26 ወጥተውም የማያውቋቸውን፣ እርሱም ያላዘዛቸውን ሌሎችን አማልክት አመለኩ፤ ሰገዱላቸውም።

27 ስለዚህ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ርግማን ሁሉ እስኪያመጣባት ድረስ፣ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቊጣ በዚህች ምድር ላይ ነደደ።

28 በአስፈሪ ቊጣና በታላቅ መዓት እግዚአብሔር (ያህዌ) ከምድራቸው ነቀላቸው፤ አሁን እንደሆነውም ወደ ሌላ ምድር ጣላቸው” የሚል ይሆናል።