ዘዳግም 32:46-52 NASV

46 እንዲህ አላቸው፤ የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ በጥንቃቄ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዟቸው፣ እኔ ዛሬ በግልጥ የምነግራችሁን ቃሎች ሁሉ በልባችሁ አኑሩ።

47 ቃሎቹ ለእናንተ ሕይወታችሁ እንጂ እንዲሁ ባዶ ቃሎች አይደሉም፤ በእነርሱ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ፤ በምትወር ሷትም ምድር ረጅም ዘመን ትኖራላችሁ።

48 በዚያችም ዕለት እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

49 ከኢያሪኮ ማዶ ባለው የሞዓብ ምድር፣ ከዓባሪም ተራሮች አንዱ ወደ ሆነው ወደ ናባው ተራራ ወጥተህ ለእስራኤላውያን ርስት አድርጌ የምሰጣትን የከነዓንን ምድር አሻግረህ ተመልከት።

50 ወንድምህ አሮን በሖር ተራራ ላይ እንደ ሞተና ወደ ወገኖቹ እንደ ተሰበሰበ ሁሉ፣ አንተም በወጣህበት በዚያ ተራራ ላይ ሙት፤ ወደ ወገኖችህም ተሰብሰብ።

51 ይህ የሚሆንበት ምክንያት ሁለታችሁም በጺን ምድረ በዳ፣ በቃዴስ በመሪባ ውሃ አጠገብ በእኔ ላይ መታመናችሁን በእስራኤላውያን ፊት ስላጐደላችሁና ቅድስናዬንም በእስራኤላውያን መካከል ስላላከበራችሁ ነው።

52 ስለዚህ ምድሪቱን ከሩቅ ሆነህ ታያታለህ እንጂ፣ ለእስራኤል ሕዝብ ወደምሰጣት ምድር አትገባም።”