19 ታላላቅ ፈተናዎችን፣ ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቅ ነገሮችን አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አንተን ያወጣበትን ብርቱ እጅና የተዘረጋች ክንድ በገዛ ዐይንህ አይተሃል። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አሁን በምትፈራቸው ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያንኑ ያደርጋል።
20 ይልቁንም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሕይወት ተርፈው፣ ከአንተ የተደበቁት እንኳ እስኪጠፉ ድረስ በመካከላቸው ተርብ ይሰድባቸዋል።
21 በመካከልህ ያለው አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ታላቅና የሚያስፈራ አምላክ (ኤሎሂም) ስለ ሆነ አያስደንግጡህ።
22 አምላክህእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እነዚህን ሕዝቦች ጥቂት በጥቂት ከፊትህ ያስወጣቸዋል፤ የዱር አራዊቱ ቊጥር በአካባቢህ እንዳይበራከት ሁሉንም በአንድ ጊዜ ማጥፋት አይፈቀድልህም፤
23 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ግን እስኪጠፉ ድረስ ከባድ ትርምስ ፈጥሮባቸው በእጅህ አሳልፎ ይሰጥሃል።
24 ነገሥታታቸውን በእጅህ ይጥላቸዋል፤ ስማቸውንም ከሰማይ በታች ታጠፋለህ። እስክትደመስሳቸው ድረስ አንተን መቋቋም የሚችል አንድም ሰው የለም።
25 የአማልክታቸውን ምስሎች በእሳት አቃጥል፤ በላያቸው የሚገኘውን ብርና ወርቅ አትመኝ፤ ለራስህ አታድርግ፤ አለበለዚያ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ዘንድ አስጸያፊ ስለ ሆነ፣ ያሰናክልሃል።