ዘፀአት 12:21-27 NASV

21 ከዚያም ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በሙሉ አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ቶሎ ሄዳችሁ ለየቤተ ሰቦቻችሁ የሚሆን ጠቦት መርጣችሁ የፋሲካን በግ እረዱ።

22 ከዚያም ጭብጥ የሂሶጵ ቅጠል በመውሰድ፣ በሳህን ውስጥ ካለው ደም ነክራችሁ የየቤቶቻችሁን ጉበንና ግራ ቀኝ መቃኑን ቀቡ። ከእናንተ አንድም ሰው እስኪነጋ ድረስ ከቤቱ አይውጣ።

23 እግዚአብሔር (ያህዌ) ግብፃውያንን ለመቅሠፍ በምድሪቱ ላይ በሚያልፍበት ጊዜ በጉበኑና በመቃኑ ላይ ያለውን ደም ሲያይ ያንን ደጃፍ አልፎ ይሄዳል፤ ቀሣፊውም ወደ ቤታችሁ ገብቶ እንዳይገድላችሁ ይከለክለዋል።

24 “እናንተም ሆነ ልጆቻችሁ ይህን መመሪያ ቋሚ ሥርዐት አድርጋችሁ ትታዘዛላችሁ።

25 እግዚአብሔር (ያህዌ) እሰጣችኋለሁ ብሎ በገባው ቃል መሠረት ወደ ምድሪቱ ስትገቡ ይህን ሥርዐት ጠብቁ።

26 ልጆቻችሁ ስለ ሥርዐቱ ምንነት ሲጠይቋችሁ፣

27 ‘ግብፃውያንን በቀሠፈ ጊዜ፣ በግብፅ ምድር የእስራኤላውያንን ቤት አልፎ በመሄድ ቤታችንን ላተረፈ፣ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የፋሲካ መሥዋዕት ነው’ ብላችሁ ንገሯቸው።” ከዚያም ሕዝቡ አጐነበሱ፤ ሰገዱም።